አዲስ መሶብ በተገልጋዮች አንደበት

You are currently viewing አዲስ መሶብ በተገልጋዮች አንደበት

“‘ፋይል አምጣ፤ ሲስተም ጠፋ በሚል መንገላታት አስቀርቷል

                                                                                          ተገልጋዮች

የሀገር እድገት ለዜጎች በሚሰጥ አገልግሎት እንደሚወሰን ሁሉ፤ ዜጎች ፈጣን አገልግሎት ካላገኙ ከግለሰባዊ እንግልት ባለፈ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል፡፡ በሀገሪቱ በየጊዜው በዜጎች ምሬት ከሚሰማባቸው ዘርፎች መካከል የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታይ ክፍተት ተጠቃሽ ነው። በተለይም የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚታዩ ችግሮች ዜጎችን ለእንግልት ሲዳርጉ ይስተዋላል። መንግስት ይህንን ችግር ለመቅረፍ የአገልግሎት ዘርፉን ለማዘመን ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ የዚህም ማሳያው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሽ ነው፡፡

በዛሬው ዝግጅታችን ትኩረት ያደረግነው በቅርቡ ወደ አገልግሎት የገባው የአዲስ ሞሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ጅማሮ ላይ ነው። እኛም አገልግሎቱ ምን እንደሚመስል ተገልጋዮችንና አገልግሎት ሰጪዎችን ከማነጋገር ባለፈ ተዘዋውረን ምልከታ አድርገናል፡፡ በምልከታችንም ማዕከሉ ለተገልጋዮችም ሆነ አገልግሎት ለሚሰጡት ባለሙያዎች ምቹ መሆኑን ለማየት ችለናል፡፡ የማዕከሉ ሰራተኞች ከታች ከእንግዳ ተቀባዮቹ ጀምሮ እስከ እያንዳንዱ ክፍል ድረስ በፈገግታ የተሞሉና የአገልጋይነት ስሜት የተላበሱ ናቸው፡፡ አገልግሎት ፈልጎ የሄደውም በጥሩ መንፈስና ያለመጨናነቅ የሚፈልገውን አገልግሎት ሲያገኝ ተመልክተናል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡን ባለጉዳዮች መካከል ወጣት ዮናታን ሚዲየም አንዱ ነው፡፡ “ወደማዕከሉ የመጣሁት የሥራ አጥ ለማውጣት አሻራ ለመስጠት ነው። አገልግሎት አሰጣጡ እጅግ በጣም አስደሳች ነው። ያለምንም መጉላላት ተስተናግጃለሁ። 20 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አገልግሎት አግኝቻለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ወረዳ ላይ ሞክሬ ሰልችቶኝ አገልግሎቱን ሳላገኝ ነበር የተመለስኩት። ወረዳ ላይ ወረፋ ይበዛል። የሲስተም መቆራረጥ ችግርም አለ፡፡ በዚህም አገልግሎት ሰጪ ሠራተኞችም የተጨናነቁና በሥነ ስርዓት ለማስተናገድ ይቸገሩ ነበር፡፡” በማለት አስተያየት ሰጥቷል፡፡

ሌላዋ አስተያየት ሰጪያችን የቤት ውል ለማደስ መምጣታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ዘነበች መብራቴ ናቸው። በማዕከል ስላገኙት አገልግሎት በሰጡን አስተያየት፤ “በአገልግሎት አሰጣጡ ተደስቻለሁ፡፡ አይቼው የማላውቀው አገልግሎት ነው ያገኘሁት። ቀደም  ሲል አገልግሎት የማገኘው በተልዕኮ ነበር፡፡ ምክንያቱም እግሬ በብረት የተያዘ በመሆኑ  አገልግሎት የሚሰጥበት ቢሮ መድረስ አለመቻሌ ነው፡፡ ጉዳዬን ለመፈጸም በሰው ተልዕኮ ከመሆኑም በላይ ረጅም ሰዓት እቀመጥ ነበር፡፡ አሁን በዚህ ማዕከል ግን ራሴ በአሳንሱር (በሊፍት) ወጥቼ ጉዳዬን በአካል ለማስፈጸም ችያለሁ። በፍጥነትም አገልግሎት አግኝቻለሁ። ቀደም ሲል የነበረው የአገልግሎት  አሰጣጥ ለአቅመ ደካማና አካል ጉዳተኞች ምቹ አልነበረም። አገልግሎት አሰጣጡ ሁሉንም አይነት የህብረተሰብ ክፍል በእኩል ደረጃ ማስተናገድ በሚያስችል ሁኔታ ነው የተሰራው። አገልግሎት አሰጣጡ በዚህ ደረጃ መሻሻሉ መልካም ነው፡፡ በዚሁ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ለዚህም  እናመሰግናለን” 

ወደ ማዕከሉ የልደት ካርድ ላይ ማህተም ለማስደረግ የመጡት አቶ ሀይሉ ጥበበ በበኩላቸው፤ “የአገልግሎት አሰጣጡ ሳቢ ነው፡፡ ከአቀባበል ጀምሮ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት አሰጣጥ ነው ያለው፡፡ በመንግስት ተቋም ውስጥ እንዲህ አይነት አገልግሎት አግኝቼ አላውቅም፡፡ ይህ የመጀመሪያዬ ነው። ቀኑን ሙሉ አልፎ ተርፎም ሁለት እና ሦስት ቀናት ይፈጅ የነበረውን አገልግሎት አሁን ላይ በደቂቃዎች ማግኘት በመቻሌ እጅግ በጣም ተደስቻለሁ። ከክፍያ ጋር ተያይዞም የሚያጋጥም ችግር የለም፡፡ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት የተለያዩ ባንኮች አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ከባድና ውስብስብ ነበር፡፡ በፀሀይና በብርድ መጠበስ እንዲሁም ላላስፈላጊ የገንዘብና የጊዜ ብክነት ያጋልጥ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከነዋሪነት መታወቂያ እና የልደት ካርድ ጋር ተያያዥ የሆኑ አገልግሎቶችን ወረዳ ላይ ለማግኘት ወረፋ ይያዝ የነበረው ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት እስከ 11፡00 ሰዓት ሰልፍ በመያዝ  ነበር፡፡ ለወረፋ ማስያዣም አላስፈላጊ ወጪ እናወጣ ነበር፡፡ አሁን ያለው አሰራር ግን እንግዳ ለማስተናገድ ሳቢ ነው፡፡ እንዲሁም የሠራተኞቹም አቀባበል መልካም ነው” የሚል ሃሳብ እና አስተያየት አጋርተውናል፡፡

 ሌላው የማዕከሉ ተገልጋይ አቶ ሰለሞን አየለ ሲሆኑ፤ የመጡበት ዓላማም የቤት ውል ለማሳደስ እንደሆነ በመጠቆም በማዕከሉ ስላገኙት አገልግሎት እንዲህ ብለዋል፤ “ተስተናግጄ ለመውጣት 20 ደቂቃም አልፈጀብኝም፡፡ አገልግሎቱን ለማግኘት ወረዳ ላይ ሞክሬ ወደ ክፍለ ከተማ ቢልኩኝም ቀኑን ሙሉ ፈጅቶብኝ ሳይሳካልኝ ተመልሻለሁ፡፡ እዚህ ተቋም ውስጥ ግን በደቂቃዎች መገልገል ችያለሁ። የእንግዳ መቀመጫ ወንበሩ፣ የቢሮው ውበትና ንጽህና የአገልግሎት ሰጪዎቹ አቀባበል ማራኪ ነው፡፡ ʻፋይል አምጣ፣ ሲስተም ጠፋ’ እየተባለ መንገላታት የለም፡፡ ደስተኛ ሆኛለሁ። ማንኛውም ሰው ያለምንም ችግር እየተስተናገደ ነው። ይህንን የአሠራር ስርዓት የዘረጋውን መንግስትን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡”

ወይዘሮ መዓዛ ታደሰ በአዲስ መሶብ አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ውስጥ የገቢ ቢሮ ቡድን መሪ ናቸው። አንደሳቸው ገለጻ፤ በክፍላቸው የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (ቲን ነምበር) ምዝገባና የተለያዩ አገልግሎቶች ይሰጣሉ። ለነጋዴ፣ ለተቀጣሪ፣ ለማህበራት ቲን ነምበር ከ30 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይሰጣል። የሚስተናገድበት አካባቢ በራሱ ምቹ ነው፡፡ ምቹ መሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ይረዳል። ከዚህ ቀደም ይህ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው በየክፍለ ከተማው ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ የቦሌ ነዋሪ ቲን ነምበር ማግኘት የሚችለው በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ብቻ ነበር። አሁን ላይ ግን በመሶብ አገልግሎት የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ ሰው ሁሉ የሁሉንም አገልግሎት በማዕከሉ ማግኘት ይችላል። በዚህ አሰራር ጊዜን እና ገንዘብን እንዲሁም አቅምን መቆጠብ ተችሏል፡፡

ክፍለ ከተማና በዚህ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጡ ልዩነት አለው። ክፍለ ከተማ ቲን ነምበር ለማውጣት ሲፈለግ የተለያዩ ሴክተሮች ይኬዳል። ለምሳሌ ማህበራት ቲን ነምበር ለመውሰድ ከስራና ክህሎት ይጀመራል፡፡ በስራና ክህሎት ውስጥ መደራጀት ደንብና መቋቋሚያ አዋጅ ጨርሶ መምጣት ይኖርበታል፡፡ ከዛ በኋላ ነው ወደ ገቢዎች የሚመጣው። ከገቢዎች ደግሞ ወደ ንግድ ቢሮ ይሄዳል። በዚህ አማካኝነት በማዕከሉ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ቢሮ ውስጥ አግኝቶ ይመለሳል፡፡ ምልልሱን ያስወግድለታል፡፡ ከእንግልት የጸዳ አገልግሎት ከማግኘቱም በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት አግኝቶ በጊዜ ይመለሳል፡፡  

 ቡድን መሪዋ አክለው እንዳብራሩት የተዘረጋው ሲስተም በራሱ ምቹ ነው፡፡ የተሟላ መሰረተ ልማት ተዘርግቶለታል። በማንኛውም ሰዓት ለተገልጋይ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ሲስተሙ አግዞናል፡፡ አሁን በምንሰጠው አገልግሎት ተገልጋይ እረክቶና ተደስቶ ነው እየሄደ ያለው፡፡ ክፍለ ከተማ ግን የነበሩት መሰረተ ልማቶች አገልግሎት ለመስጠት ምቹ ስላልነበሩ የተገልጋይ እንግልትና መመላለስ ይበዛ ነበር፡፡

አቶ ኤፍሬም አሰፋ በማዕከሉ በሥራና ክህሎት የኢንተርፕራዞች ድጋፍ ባለሙያ ናቸው፡፡ እንደባለሙያው ገለጻ፤ የባዮሜትሪክስ ኪትስ አገልግሎት (እንደ ብሔራዊ መታወቂያ አሻራ በመውሰድ የአንድን ሰው መረጃ የሚይዝ) እየሰጡ ናቸው፡፡ ከብሔራዊ መታወቂያ የሚለየው አንድ ሰው መጥቶ ሲመዘገብ የሥራ አጥ ካርድ ቁጥር ይሰጠዋል፡፡ የሚሰጠው አገልግሎትም የተለያዩ ሥራዎች ወይንም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ማስታወቂያዎች ሲለቀቁ (ፖስት ሲደረጉ) አገልግሎቱን በቀላሉ ለማየት ይጠቅመዋል፡፡ ይህ አገልግሎት በአዲስ አበባ በሁሉም ወረዳዎች ይሰጣል፡፡ ወረዳ ላይ ከሰው መብዛት እና ከመሰረተ ልማት አለመሟላት ጋር ተያይዞ ተገልጋዮች ተገቢውን አገልግሎት ሳያገኙ ይመለሳሉ፤ ይጉላላሉ፡፡ ከሄደበት ወረዳ አንድ አገልግሎት ካገኘ በኋላ ሌላ አገልግሎት ለማግኘት ሌላ ቦታ መሄድ ይጠበቅበታል። ለአገልግሎት ሰጪው ባለሙያም አድካሚ ነበር፡፡ ተደጋጋሚ ድካምም መሰላቸትን በመፍጠር ደንበኛን በሚገባው ልክ ያለማስተናገድ ችግር ይስተዋል ነበር፡፡

በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ግን ፈጣን ነው፡፡ 10 ደቂቃ ባልፈጀ ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ መደራጀት ለሚፈልጉ ተገልጋዮች ንግድ ፍቃዱንና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (ቲን ነምበሩን) የመደራጀት ሂደቱንም በተመሳሳይ ቦታና በአጭር ጊዜ ውስጥ ጨርሶ ይወጣል፡፡ በሲስተም የተደገፈ በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት አግኝተው ይሄዳሉ፡፡ በቴክኖሎጂ መጠቀም ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ስለሚያስችል በወረዳ አንድ ሰው እናስተናግድ የነበረውን 3 እና 4 ሰው ለማስተናገድ ያስችላል፡፡ ቴክኖሎጂ መጠቀም በራሱ በራስ መተማመን ያጎለብታል እንደ ባለሙያው ገለጻ፡፡ የተገልጋይ እርካታን ማየትም ሌላው ተደራራቢ ምቾት ነው፡፡

 አቶ ቃሉ አቤል በተመሳሳይ በማዕከሉ የመንግስት ቤት አስተዳደር ባለሙያ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። የቤት አስተዳደር ስራ አገልግሎት ቤት ከመመዝገብ ባለፈም ከወሳኝ ኩነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቤተሰብን ስለሚመለከት ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ብዙ ፋይሎችን ማየት ይጠበቅብን ነበር ይላሉ፡፡ ሌላው ችግር የመረጃ አደረጃጀቱ የተሟላ አልነበረም፡፡ በዚህም የመረጃ መዛባትና የፋይል መጥፋት ያጋጥም ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን በውል ቁጥሩ ወይንም በቤት ቁጥር አሊያም በባለቤቱ ስም መረጃውን በመፈለግ ፋይሉን በቀላሉ በማግኘት የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንዳስቻላቸው ነው የሚገልጹት፡፡ የመንግስት ቤት አስተዳደር ዲጂታላይዝድ በመደረጉ ቀደም ሲል የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል፡፡ አንድ የቤት ባለንብረት፣ የመንግስት ቤት ተከራይ ቤቱ ሲስተም ላይ በመመዝገቡ ምክንያት ፋይል ጠፍቷል ሌላ ጊዜ ናቶሎ የሚባልበት ነገርን አስቀርቷል፡፡ ስለዚህ የተገልጋዮችን እንግልት እንዲሁም የአገልጋዩን ድካም ሙሉ በሙሉ ያስቀረና የተገልጋይን አርካታ ያመጣ ምቹ አሰራር ው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት አፈጻጸምን በተመለከተ በተካሄደው በ3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በተደገፈ አግባብ አገልግሎትን ከማዘመን አንፃር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተሠሩ ስላሉ ሥራዎች ላይ አተኩሮ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳ ጥያቄ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ እንደጠቆሙት፤ በከተማ ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ፈጣን፣ ቀልጣፋና ምቹ በሆነ አግባብ ለተገልጋዩ ተደራሽ የማድረግ ዓላማ ያለው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በማዕከል እና በቅርንጫፍ ደረጃ ተጀምሯል። በዚህም በማዕከል 107  እንዲሁም በቦሌ ቅርንጫፍ ደግሞ 96 በድምሩ 2013 አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ ሆነው በኦንላይን እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ማዕከላት የተመደቡ ባለሙያዎች 70 በመቶ አዲስ ምሩቅ ሲሆኑ፤ ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት ተገቢውን ስልጠና ወስደዋል፡፡ ከነባር ሠራተኞች ጋር ተዋህደው እንዲሠሩ በቂ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review