የመዲናዋ አንኳር ኪነ ጥበባዊ መረጃዎች

You are currently viewing የመዲናዋ አንኳር ኪነ ጥበባዊ መረጃዎች

ባሳለፍነው ሳምንት በመዲናዋ አዲስ አበባ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ። ከተሰናዱት ዋና ዋና ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የመጽሐፍት ምርቃት፣ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ ጥበባዊ ውይይቶች፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡ 

መጽሐፍት

“ዋናተኛ ፀሃይ” መጽሐፍት ለንባብ በቃ። በደራሲ ኤልሳ ሙሉጌታ የተደረሰው “ዋናተኛ ፀሃይ” የተሰኘው መጽሐፍ ባሳለፍነው ሳምንት ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉ በተለያዩ የመጽሐፍት መደብሮች ውስጥ ይገኛል ተብሏል፡፡ ደራሲዋ ከዚህ ቀደም ‘ሃምራዊ ተረኮች’ የተሰኘ የአጫጭር ልብወለዶች ስብስብ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቷ የሚታወስ ነው፡፡

የወጣቷ ገጣሚ የመንበረ ሃይሉ ‘የውበት ሰሌዳ’ የግጥም መጽሐፍ ይመረቃል፡፡ በቅርቡ ለንባብ የበቃው የውበት ሰሌዳ መጽሐፍ፣ ዛሬ 10፡00 ጀምሮ መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን /አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን  ፊት ለፊት በሚገኘው በጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል ውስጥ ይመረቃል። በምርቃቱም የተለያዩ ደራሲያንና የጥበብ ሰዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡

‘ካፌ ጎልጎታ’ መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው፡፡ በወጣቱ ደራሲ ይስሃቅ አብርሃም የተጻፈው ካፌ ጎልጎታ መጽሐፍ በመጪው ሳምንት ለንባብ እንደሚበቃ የመጽሐፉ አሳታሚ ዋሊያ መጻሕፍት አሳውቋል፡፡ መጽሐፉ አስቀድሞ በማህበራዊ ሚዲያ በቅድመ ሽያጭ ዘዴ ለገበያ የቀረበ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ታትሞ ለሁሉም ተደራስያን እንደሚደርስ የመጽሐፉ አሳታሚ አሳውቋል፡፡

‘የመሃላ ጉልበት’ በሚል ርዕስ ውይይት ይደረጋል፡፡ ዛሬ ከሰዓት 8፡00 ጀምሮ የመሃላ ጉልበት በሚል ርዕስ ውይይት ይደረጋል፡፡ ከተለያዩ የትምህርት መስኮች የተወጣጡ ምሁራን የመወያያ መነሻ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ውይይቱን ያሰናዳው ዋሊያ መጽሐፍት አሳታሚ ሲሆን፣ ውይይቱ የሚደረገው ደግሞ አራት ኪሎ ኢክላስ ህንጻ አራተኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው የዋሊያ መጽሐፍት አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡

ሥዕል

የአንጋፋው ሰዓሊ ወርቁ ማሞ ልጅ በሆነቸው በወጣቷ ሰዓሊ ገብርኤሏ ወርቁ ማሞ የተዘጋጁ የሥዕል ስራዎች የቀረቡበት “ከልብስ ባሻገር” የሥዕል አውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ የሥዕል አውደ ርዕዩ ባሳለፍነው ሳምንት በአርታዊ የሥዕል ማሳያ ውስጥ ለእይታ በቅቷል፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ ፊታችን ጥቅምት 29 ቀን 2018 ዓ.ም በእይታ ላይ ይቆያል ተብሏል።

“ኑ እንጫወት ልብ እንጠግን” ልዩ መርሐግብር ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል አማካኝነት ተዝናኖትን መነሻ በማድረግ የህጻናትን ልብ ለመጠገን ያለመ የገቢ ማሰባሰቢያ ፈስቲቫል ለሕፃናት እና ለታዳጊዎች ተዘጋጅቷል። ፌስቲቫሉ ልባቸውን ለመታከም ወረፋ በመጠበቅ ላይ ላሉ ሕፃናት ገቢ ለማሰባሰብ እና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ኢቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል፡፡ ለሕጻናት እና ለታዳጊዎች የተዘጋጀው ፌስቲቫሉ ዛሬ ቅዳሜ ረፋድ ላይ በአምባሳደር ፓርክ ከጠዋት 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።

ቴአትር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ፡፡ 12ቱ እንግዶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:30 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል፡፡ 11፡30 ደግሞ ባሎችና ሚስቶች  የተሰኘው ቴአትር በዚያው በብሔራዊ ቴአትር ይታያል፡፡እሁድ በ8፡30 ደግሞ ንጉሥ አርማህ ቴአትር እንዲሁም  እምዩ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በዚሁ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል፡፡

በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ደግሞ እሁድ በ8:00 የደመና ዳንኪረኞች የተሰኘው ቴአትር ይታያል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ ቀናት በብሄራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሦስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በቴአትር  ቤቱ ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ።፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review