የዝግጅት ክፍላችን ከማለዳው 2፡00 ሰዓት ላይ ነበር በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ማይጨው ጤና ጣቢያ የሚሰጠውን የቅድመ ጤና መከላከል ትምህርት ለመቃኘት የተገኘው፡፡ በእናታቸው ጀርባ ከታዘሉ ህፃናት እስከ አረጋውያን በጠዋቱ ጤናን ፍለጋ ተሰባስበዋል፡፡ ለህክምና በመጡበትም አጋጣሚ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ ከጤና አጠባበቅ እስከ መድኃኒት አጠቃቀም በዘርፉ እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች ይማራሉ። የሚሰጠውን ቅድመ የጤና ትምህርት ሁሉም ጆሮውን ሰጥቶ ያዳምጣል፤ ጥያቄ ያለውም ይጠይቃል፡፡ የህክምና ባለሙያዎቹም ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ በመስጠት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ለማየት ችለናል፡፡
የጤና አጠባበቅ ትምህርቱን ከሚከታተሉት ውስጥ ለህክምና ወደ ጤና ጣቢያው ከመጡት መካከል መምህርት አብነት ተሾመ አንዷ ናቸው። እንደ እሳቸው አስተያየት ጠዋት ጠዋት የሚሰጠው የጤና አጠባበቅ ትምህርት በቦታው ተገኝተን ለተማርነው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብ፣ ለጎረቤት እንዲሁም እንደ እኔ መምህር ለሆነ ደግሞ ለተማሪዎቹም ጭምር የሚተርፍ ነው ሲሉ ጠቀሜታውን ገልፀውታል፡፡
“ዛሬ በተማርኩት የማህፀን በር ካንሰር እድሜያቸው ለአቅመ ሄዋን ሳይደርስ የግብረ ስጋ ግንኙነት ለሚያደርጉ ወጣት ተማሪዎቼ እንዴት መከላከል እንዳለባቸው ለማሳወቅ ዝግጁ ነኝ። ራሳቸውን ከእርግዝና ብቻ ሳይሆን ከበሽታም እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው የተማርኩትን አስተምራቸዋለሁ” ይላሉ፡፡
“ታምሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” እንዲሉ የህክምና ባለሙያዎች የሚያስተላልፉልንን የጤና ትምህርት እና የመድኃኒት አጠቃቀም ጭምር በአግባቡ ተግባራዊ ካደረግን በሽታን መከላከል እንዲሁም ከታመምንም በቶሎ ታክመን መዳን የምንችልበት እድል ሰፊ ነው ሲሉ የጤና ትምህርቱን ፋይዳ ነግረውናል፡፡
የመምህርቷን ሃሳብ የሚጋሩት ወይዘሮ በላይነሽ ዳዲም ልጆቻቸውን ወልደው ያሳደጉት በዚሁ ጤና ጣቢያ ነው፡፡ ለክትትልም ይሁን ለህክምና ሲመጡ ጤናቸውን እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ግንዛቤ አግኝተው እንደሚሄዱም ይናገራሉ፡፡ የሚሰጠው የጤና ትምህርት አንድ ሰው ራሱን ከበሽታ ለመከላከል፣ ሲያመው መቼ ወደ ጤና ጣቢያ መሄድ እና መድኃኒቶችን እንዴት መጠቀም እንዳለበት ሙሉ መረጃ የሚሰጥ ነው ያሉት ወይዘሮዋ፤ ከዚህ በፊት በተሰጣቸው የማህፀን በር ካንሰር ትምህርት ቅድመ ምርመራ አድርገው ራሳቸውን እንዳወቁ ያስታውሳሉ፡፡ ከዚህም አልፈው አንድ ጎረቤታቸውን ምርመራ እንድታደርግ እንዳደረጓት ገልፀዋል፡፡
ሌላኛው በጤና ጣቢያው የሚሰጠው የጤና ትምህርት ለእሳቸውና ለቤተሰባቸው እንደጠቀማቸው የተናገሩት ደግሞ በልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጤና ፅህፈት ቤት በተክለ ኃይማኖት ጤና ጣቢያ ተገልጋይ የሆኑት አቶ ካህሳይ ሃይሌ ናቸው፡፡ በጤና ጣቢያው ብዙ ጊዜ ለምርመራና ለህክምና በሚመጡበት ወቅት የጤና አጠባበቅ ትምህርት ይከታተላሉ። “የተማርኩትን የጤና አጠባበቅ ትምህርት ለባለቤቴ እና ለልጆቼ ማታ ላይ እነግራቸዋለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ ጨው አብዝተው እንዳይጠቀሙ አደርጋለሁ፣ ንፅህናዬን እጠብቃለሁ፣ ጠዋት እና ማታም እንቅስቃሴ አደርጋለሁ” ሲሉ ነው የተማሩትን በተግባር እየኖሩት እንደሆነ የተናገሩት፡፡
በጤና ጣቢያው የጤና ትምህርት ከሚሰጡ ባለሙያዎች ውስጥ ሲስተር ስንታየሁ ታደሰ አንዷ ናቸው፡፡ “በሽታን ከማከም ይልቅ አስቀድሞ መከላከል ላይ መስራቱ የበለጠ ጠቀሜታ አለው። ለዚህም በጤና ጣቢያችን ሁልጊዜም ጠዋት ለህክምና የሚመጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ይፈጠርላቸዋል፡፡ ዓላማውም ማህበረሰቡ ራሱን ከበሽታ እንዲከላከል እና ጤናማ ኑሮ እንዲኖር ነው” ይላሉ፡፡
በማይጨው ጤና ጣቢያ ሲያስተምሩ ያገኘናቸው የፋርማሲ ኃላፊ ወይዘሮ ትዕግስት ሰለሞን በበኩላቸው፤ ታካሚዎችም ሆነ አስታማሚዎች ወደ ጤና ጣቢያው ሲመጡ ህክምና አግኝቶ ብቻ መሄድ ሳይሆን የመድኃኒት አጠቃቀምና የሚያስከትለውን የጎንዮሽ ጉዳት በጠዋቱ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ላይ ይማራሉ፡፡ ለህክምናም ሆነ ታካሚን ይዘው የሚመጡ ጤና እና ጤና አጠባበቅ ጉዳዮች ላይ የተማሩ እና ሙሉ በሙሉ የሚያውቁ ባለመሆናቸው ለህክምና በመጡበት ወቅት ጤናቸውን እንዲጠብቁ እና ቀድመው በሽታን መከላከል እንዲችሉ የጠዋት ትምህርቱ ያግዛቸዋል፡፡ በጤና ጣቢያው ከሰኞ እስከ አርብ በሚሰጠው የጤና አጠባበቅ ትምህርት የተለያዩ ሰዎች ስለሚስተናገዱ ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰቦቻቸው፣ ለጎረቤቶቻቸው እና ለአካባቢው ሰዎች ሳይቀር ያወቁትን እንዲያሳውቁ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡
በጤና ጣቢያው የጤና አጠባበቅ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሲስተር ራሄል ታምሩ እንደሚናገሩት የጤና አጠባበቅ ትምህርት በሽታ በመከላከል ረገድ አስተዋፅኦው የጎላ ነው፡፡ ትምህርቱ ከጠዋቱ 2፡05 ሰዓት አንስቶ እስከ 2፡30 ሰዓት ድረስ ይሰጣል፡፡ በዋናነት ለህክምና የሚመጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን በተለያየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች በተለይም በክትባት ጥቅሞች፣ የማህፀን በር ካንሰር፣ የስኳር በሽታ ምንነትና መቆጣጠሪያ መንገዶቹ፣ የደም ግፊት፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች፣ የመድኃኒት አጠቃቀም እና የጎንዮሽ ጉዳት፣ የንፅህና አጠባበቅ፣ የእርግዝና መከላከያ መንገዶች እንዲሁም ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ይሰጣሉ፡፡
ጤና ጣቢያው በዓመት ቁጥራቸው 32 ሺህ የሚሆኑ ተጠቃሚዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ እያንዳንዱ ሰው በዓመት ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚህም በቀን ከ150 እስከ 200 የሚሆኑ ታካሚዎች አገልግሎቱን ያገኛሉ፡፡
እንደ ሲስተር ራሄል ገለፃ፣ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ማህበረሰቡ በሽታ መከላከል ላይ ያለውን ንቃተ ህሊና በማሳደግ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ከዚህ በፊት መድኃኒት የሚያቋርጡ በአግባቡ መድኃኒታቸውን መውሰዳቸው፣ የግልና አካባቢ ንፅህናቸውን መጠበቃቸው እንዲሁም ማህበረሰቡ ጥያቄዎች በመጠየቅ ግብረ መልሶችን መቀበሉ ለማሳያነት መጥቀስ እንደሚቻል አንስተዋል፡፡
የተክለ ኃይማኖት ጤና ጣቢያ ለሁለት ወረዳ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በዓመት 107 ሺህ የማህበረሰብ ክፍሎች ይስተናገዳሉ ያሉት የጤና ጣቢያው ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ ከተማ አለሙ ናቸው፡፡
የጤና ትምህርት የጤና ሁሉ መሰረት ነው፡፡ ምክንያቱም የጤና ትምህርት ሲሰጥ ሰዎች ሊደርስባቸው ከሚችለው የጤና ችግር ራሳቸውን የሚከላከሉበት ነው፡፡ የሀገራችንም የጤና ፖሊሲ መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለዚህም ጤና ጣቢያችን ከሰኞ እስከ አርብ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ደም ግፊት፣ ስኳር፣ ካንሰር እና ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች እና የንፅህና አጠባበቅ ላይ ትምህርቶችን ይሰጣል፡፡
ጤና ጣቢያው የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ እየተጋ እንዳለ የሚናገሩት አቶ አለሙ፤ ከጠዋቱ ትምህርት በተጨማሪ ማንኛውም አገልግሎት ፈልጎ የመጣ ታካሚ መጀመሪያ እንደገባ የደም ግፊት ልኬት እንደሚደረግለት እና እራሱን የሚያውቅበት ሁኔታ እንዳለ ነው የነገሩን። ባለሙያዎችም እቅድ ከማውጣት ጀምሮ ተዘጋጅተው በማስተማር ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ የተማሩትም ትምህርት ላልተማሩት ቤተሰብና ጎረቤቶቻቸው ለማስገንዘብም በራሪ ወረቀቶች ያድላሉ። ጤና ጣቢያው በየቀኑ ምን ያህል በራሪ ወረቀቶች እንደተበተኑም ክትትል በማድረግ ይመዘገባል ብለዋል፡፡
መንግስት የዜጎችን ጤና ለማስጠበቅ ሲታትር የማህበረሰቡን ኃላፊነት በተመለከተ በቅድሚያ የራሱን ጤና መጠበቅ፣ ከጤና ባለሙያዎች የሚያገኘውን መረጃ ለሌላው ማካፈል፣ የተሰጠውን ትምህርት በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል ሲሉም ይመክራሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በሽታ መከላከል እና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት የጤና አጠባበቅ ትምህርት ባለሙያ መርሻ ወልደገብርኤል እንደገለፁት እንደ ሀገር የምንከተለው የጤና ፖሊሲ ቅድመ የጤና መከላከል ፖሊሲ ነው፡፡ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና አጠባበቅ ትምህርቱም የተጀመረው የጤና ኮሌጆች ከተጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡
አዲስ አበባ ከተማም ይህንኑ የጤና ፖሊሲ ለማሳካት እየሰራች ትገኛለች። በከተማዋ በሁሉም ጤና ጣቢያዎች መከላከልን መሰረት ያደረጉ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጠዋት የሚሰጠው የጤና ትምህርት አንዱ ነው። አሁን ላይ ሚዛኑን እየደፋ የመጣው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት እንደ ስኳር፣ ካንሰር፣ የደም ግፊት፣ የጡትና የማህፀን በር ካንሰር የመሳሰሉት እና ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ላይ እንዴት መቆጣጠር እና መከላከል እንደሚቻል ትምህርቱ እየተጠ ይገኛል፡፡
የጤና ትምህርቱን ወደ ማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በከተማዋ ባሉ ሁሉም ጤና ጣቢያዎች ትምህርቱ እንደሚሰጥ የገለፁት አቶ መርሻ፤ ማህበረሰቡ ጤና ላይ ያለው ግንዛቤ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ጤናውን ሊጎዱ ከሚችሉ ችግሮች ራሱን እንዲጠብቅ ማድረግ ዋናው ዓላማችን ነው፡፡ ይህም ጤናማ ማህበረሰብን ከመፍጠር በተጨማሪ ለህክምና የሚወጡ ወጭዎችንም የሚቀንስ ነው፡፡
እንደ ጤና ቢሮ ለጤና ተቋማት ሁለት አይነት ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ይህም የድንገተኛ ክትትል አንዱ ሲሆን፤ ጤና ጣቢያዎች በጠዋቱ የጤና አጠባበቅ ትምህርት ላይ እቅድ መያዛቸውን፣ ተጨባጭ በሆኑ መርጃ መሳሪያዎች መጠቀማቸውን፣ በሰዓቱ ማስተማራቸውን እና በሚገባቸው ቋንቋ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ሙሉ ክትትል ይደረጋል፡፡ ሁለተኛው ክትትል ደግሞ በየሩብ ዓመቱ ክትትል በማድረግ ግብረ መልስ ይሰጣል። በእነዚህ መነሻነትም ሁሉም የክፍለ ከተማ ኃላፊዎች በተገኙበት የተሻለ ስራ የሰሩ እና ያልሰሩ ባለሙያዎችን በመለየት መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች እንዲያሻሽሉ ይደረጋል፡፡
የጤና አጠባበቅ ግንዛቤ ፈጠራው በጥናት የተደገፈ ባይሆንም ከበፊቱ በተሻለ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የተናገሩት አቶ መርሻ፤ ለዚህም በምሳሌነት የጠቀሱት፤ ማህበረሰቡ የራሱን እና የአካባቢውን ንፅህና እየጠበቀ መሆኑ፣ የእያንዳንዱን በሽታዎች ምንነት እና ምን ማድረግ እንዳለበት እንደሚመልስ እና የኤች. አይ.ቪ ኤድስ ስርጭት መቀነሱን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
የባህሪ ለውጥ የሚያመጣው የግንዛቤ ፈጠራ ውጤት ነው የሚሉት አቶ መርሻ ለወደፊትም የማህበረሰቡን የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የግንዛቤ ፈጠራው ላይ በሰፊው ይሰራል፡፡ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የረጅም ጊዜ ስራ የሚፈልግ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በጤና ትምህርቱ የመጣውን የባህሪ ለውጡን ለማወቅም ወደፊት ጥናት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ