ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሳርቤት – ጀርመን አደባባይ- ጋርመንት ፉሪ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባላት በተገኙበት መርቀዉ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸዉን ገለጹ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሳርቤት – ጀርመን አደባባይ- ጋርመንት ፉሪ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባላት በተገኙበት መርቀዉ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸዉን ገለጹ

AMN ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ከሳርቤት – ጀርመን አደባባይ- ጋርመንት ፉሪ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) እና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባላት በተገኙበት መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሕዝባችንን በታማኝነት፣ በቅንነት ለማገልገል የገባነውን ቃል ቆጥረን እየተገበርን እንገኛለን። የተሰሩት መሰረተ ልማቶች ከተማችንን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት፣ ለዜጎቻችን ሰፊ የስራ ዕድል የፈጠረ እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ መሰረታዊ የሆነ ለዉጥ ማምጣት በሚያስችል መልኩ የተሰራ ነው።

በልማቱ ከመሬት በላይ ከሚታየው እኩል ከመሬት በታች ጭምር የተሰሩ በርካታ ስራዎች የከተማችንን አገልግሎት የሚያሳልጥ፣ በዘላቂነት ስማርት ሲቲ ለማድረግ የሰነቅነዉን ራዕይ ለማሳካት የሚያስችል መሰረታዊ ስራ የተሰራበት፣ ሰፊ የስራ ዕድል የተፈጠረበት ሲሆን፤ ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ እሴት፤ የስበት ማዕከል የሆኑ ፅዳት፣ ውበት፣ አገልግሎትን ያጣመሩ ስራዎችም በስፋት ተሰርተውበታል ብለዋል፡፡

ይህ የኮሪደር ልማት በሁለተኛ ዙር ከጀመርነው 6ኛዉና ከካዛንቺስ ኮሪደር ቀጥሎ በከተማችን ሁለተኛው ረጅሙ እና ሰፋ ያለ አካባቢ የሚሸፍነው ሲሆን ከ589 ሄክታር በላይ ቦታ የለማበት ነው።

• እስከ 60 ሜትር የሚሰፋ 16.5 ኪ.ሜ አስፓልት መንገድ ( በተጨማሪ 3 .5 ኪ. ሜ የውስጥ ለውስጥ መንገድ) አለው ፣

• 33 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ ፣

• 13.3 ኪ.ሜ የሳይክል መንገድ ፣

• 21 የተለያዩ ፕላዛዎች ፣

• ክረምት ከበጋ ፣ በቀን እና በምሽት አገልግሎት የሚሰጡ 20 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣

• 20 የልጆች መጫወቻ ቦታዎች ፣

• 5.2 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ፣

• 20 የመኪና ማቆሚያ ቦታና ተርሚናሎች ፣ 1 የመኪና ቻርጂንግ ስቴሽን ፣

• በግለሰቦች እና በመንግስት የተገነቡ 1,107 የንግድ ቤቶች ፣

• 50.5 ሄክታር ስፋት ያላቸዉ አረንጓዴ ቦታዎች ፣

• 40 የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች ፣

• 38 የታክሲና አውቶቡስ ቤይ ፣

• 13 ካፌዎች እና 1 ሬስቶራንት እንዲሁም ከ 1 ሄክታር በላይ የነርሰሪ ቦታን በዉስጡ አካትቶ ይዟል ብለዋል፡፡

ይህንን ለከተማችን ተጨማሪ ድምቀት ፣ ለዜጎቻችን መጠነ ሰፊ የስራ እድል እና የእውቀት ሽግግር የፈጠረን ፣ ለነዋሪዎቿ ደግም ምቾትን ያጎናፀፈውን ግዙፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በታለመለት ጊዜ በጥራት እና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ላደረጋችሁ ፣ ከመደበኛ ስራችሁ ጎን ለጎን ሌት ተቀን ለለፋችሁ በየደረጃዉ ያላችሁ የከተማችን አመራሮች፣ ባለሞያዎች፣ እንዲሁም በልማት ስራው ሁልጊዜም የዘወትር ድጋፍ እና ትብብሩ ላልተለየን የአካባቢው ነዋሪ ማህበረሰብ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review