ምርቶችን በስፋት በመሰብስብ ያልተቋረጠ የምርት አቅርቦት እና የተረጋጋ የግብይት ስርዓት እንዲፈጠር የተጀመሩት ገበያን የማረጋጋት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታቋል፡፡
አምራች እና ሸማቹን በማስተሳሰር፣ የመዲናዋ ነዋሪዎች የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እና በተረጋገጠ ጥራት ምርቶችን እንዲያገኙ ከተማ አስተዳደር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
በከተማዋ የሚገኙ ሕብረት ስራ ማህበራት በቂ ምርቶችን ወደ ከተማዋ በማስገባት፣ የዋጋ ንረትን በማስቀረት ገበያን ከማረጋጋት በዘለለ፣ የምርት እጥረትም እንዳይፈጠር የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
በተንዛዛ የግብይት ሥርዓት እና ሰንሰለት ምክንያት በሸማቹ የመዲናዋ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጠረውን አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በማስቀረት በኩልም የእነዚህ ማህበራት ሚና የጎላ መሆኑም ተገልጿል።
ማህበራቱ ከግብርና እስከ ኢንዱስትሪ ምርት ለሸማቹ በማድረስ የሸማቹን ፍላጎትና የመግዛት አቅም ታሳቢ በማድረግ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረባቸውን አጠናክረዉ ቀጥለዋል፡ የማህበራቱም የምርት አቅርቦት በአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን አመራሮች ተጎብኝቷል፡፡

የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ሽታዬ መሃመድ በተከናወኑት ተግባራት ማለትም በሁሉም ሸማች ማህበራት በኩል በቂ የግብርናና የኢንዱስትሪ እንዲሁም የምርት ክምችት እንዲኖር ማስቻሉም ተጠቅሷል፡፡
በዚህም፣ ማህበራቱ የተለያዩ ምርቶች ላይ የተለያዩ እሴቶችን በመጨመር በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረቡ እንደሚገኙም ነው የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሀብተየስ ድሮ የተናገሩት፡፡
ከሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ምርቶችን በጥራት እና በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙ መሆናቸውን ሸማቾች ጠቁመዋል፡፡
በቴዎድሮስ ይሳ