ብልጽግና ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር እንዲያረጋግጥ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና አባላት በመልካም ስነምግባር ኃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

You are currently viewing ብልጽግና ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር እንዲያረጋግጥ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና አባላት በመልካም ስነምግባር ኃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

‎AMN ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም

‎ብልጽግና ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር እንዲያረጋግጥ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና አባላት በመልካም ስነምግባር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

‎የብልፅግና ፓርቲ የስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች እና ልዩ ልዩ የፓርቲ አጀንዳዎች ላይ መክሮ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን ተከትሎ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

‎ማብራሪያውን የሰጡት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አደም ፋራህ እንደተናገሩት ፣ከተሰጡ አቅጣጫዎች አንዱ የፓርቲ አባል እና አመራሮችን በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት የመገምገም እና የመመዘን ስራ እንዲሰራ አቅጣጫ መቀመጡን ገልፀዋል።

‎በዚህ አቅጣጫ መሰረት የፓርቲውን አመራሮች እና አባላት በደረጃው የመመዘን ስራ መሰራቱን ገልፀው፣ ምዘናውን ተከትሎ እውቅናና ምስጋና የተሰጣቸው መኖራቸውን አስረድተዋል።

‎በስነምግባር እና በተግባር አፈፃፀማቸው ድክመት የታየባቸው 8ሺህ 613 አባላት ላይ ተገቢውን የዲሲኘሊን የእርምት እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

‎የተወሰደው እርምጃ ከሀላፊነት ማንሳት ጀምሮ እስከ ከነበሩበት ደረጃ ዝቅ ብለው እንዲሰሩ፣ እና ሽግሽግ እስከማድረግ የሚደርስ መሆኑን አመላክተዋል።

‎ብልጽግና ፓርቲ ለህዝብ ቃል የገባውን በተግባር እንዲያረጋግጥ በየደረጃው ያሉ አመራሮችን እና አባላት በመልካም በስነምግባር ሀላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ አስረድተዋል ።

‎የሚወሰደው እርምጃ በተቀመጠው እቅድ መሰረት የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ፣ኑሮ እንዲሻሻል የአሰራር ስርዓት እንዲገነባ መሆኑን ገልፀዋል።

‎ከዚህ አንፃር በየጊዜው ግምገማዎችን እና ምዘናዎችን በማካሄድ መበረታታት ያለበት እና ተገቢውን የእርምት እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባውን ለይቶ የመሄድ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ሲሉ ምክትል ኘሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

‎በተሰጠው ሀላፊነት ህዝቡን በታማኝነት የማያገለግል የስነምግባር ችግር ያለበት በብልሹ አሰራር ፣በሌብነት ውስጥ የተዘፈቀ የፓርቲ አመራርም ሆነ አባል እርምጃ ይወሰድበታል ብለዋል።

‎ከዚህ በተጨማሪ በፓርቲው መርሆች እና እሴቶች እየተመራ የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማይንቀሳቀስ አመራር ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review