የአፍሪካ አገራት የጣና ፎረም ምክረ ሀሳቦች በመተግበር ለአህጉሪቷ ለውጥ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ የማላዊ የቀድሞ ፕሬዝዳንትና የጣና ፎረም የቦርድ አባል ጆይሴ ባንዳ ገለጹ።
በባህር ዳርና አዲስ አበባ ከተሞች ላለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 11ኛው ከፍተኛ ደረጃ ጣና ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።
“አፍሪካ በተለዋዋጩ ዓለም ሥርዓት” በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደው ፎረም፤ በአፍሪካ ሠላምና ደህንነት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ በትኩረት መክሯል።
አፍሪካ በኢኮኖሚ እንዴት ራሷን መቻል አለባት? ምን ዓይነት እርምጃዎች ያስፈልጋሉ? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ በአፍሪካ ያሉ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ አካታች ሥርዓት መዘርጋት ለነገ የሚባሉ ጉዳዮች እንዳልሆኑ በፎረሙ በሰፊው ምክክር ተካሂዶበታል።

የማላዊ የቀድሞ ፕሬዝዳንትና የጣና ፎረም የቦርድ አባል ጆይሴ ባንዳ በፎረሙ መዝጊያ ላይ እንዳሉት፤ 11ኛው የጣና ከፍተኛ ደረጃ ፎረም ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል።
የፎረሙ መሪ ሀሳብ አፍሪካ በተለዋዋጩ ዓለም ሥርዓት እንደ አህጉር ልንነጋገርበት የሚገባ ወቅቱን የጠበቀ ጽንሰ ሀሳብ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ዲጂታል የሚደረገው ሽግግር፣ የተፈጥሮ ሀብትን በፍትሃዊነት እና ዘላቂነት ተደራሽ ማድረግ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዓለም በፍጥነት እየተለወጠች መሆኑን አስታውሰው፤አፍሪካም እየተለወጠ ላለው የዓለም ሥርዓት የሚመጥን እንቅስቃሴ ማድረግ አለባት፤ ለዚህ ደግሞ በጣና ፎረም የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦችን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ከአፍሪካ አገራት በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
አፍሪካ ለማሳካት ያስቀመጠቻቸው ውጥኖች ያለ ወጣቶች ተሳትፎ እውን ሊሆን እንደማይችል አመልክተው፤በአፍሪካ በሁሉም መስክ የሚከናወኑ ተግባራት ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባ ማስገንዘባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
በፎረሙ ላይ የተለያዩ አገራት መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ልዩ መልዕክተኞች ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።