የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገበያን ለማረጋጋት እና የሸማቾችን ጥያቄ ለመመለስ ከደላላ ሰንሰለት ነፃ የሆኑ ግብይቶችን ለማሣለጥ አምራች እና ሸማቾችን በቀጥታ የሚያገናኙ፣ ጥራት እና ደረጃቸውን የጠበቁ የገበያ ማዕከላት ገንብቶ ወደ አገልግሎት በማስገባት የህብረተሰቡን ጥያቄ እየመለሰ ይገኛል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የገበያ ማዕከል ከእንስሳት ተዋጽኦ እስከ ጥራጥሬ፤ አትክልት እና ፍራፍሬ ያሉ ግብአቶች በብዛትም በጥራትም በአንድ ቦታ እየቀረቡ በመሆኑ ተጠቃሚ መሆናቸውን ሸማቾች ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።
ወ/ሮ ሰላማዊት አስቻለው በማዕከሉ ያገኘናቸው ሸማች ሲሆኑ፤በርካታ ምርቶች በአንድ ቦታ እንደሚገኙ እና በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬዎቹ ትኩስ መሆን ማዕከሉን እንዲመርጡ ምክንያት እንደሆናቸው ነው የገለፁት፡፡
ማዕከሉ በተለይም የመኪና ማቆሚያን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ያሟላ በመሆኑ በነጻነት ለመሸመት ምቹ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሌላኛው ሸማች አቶ ስለሺ ታደሰ፤ ማዕከሉ ብዙ እቃዎችን በአንድ ቦታ ለማግኘት ምቹ እንደሆነና ይህም ድካምን ጭምር የሚያቃልል መሆኑን ነው ያጫወቱን።
አቶ መካ ኑሩ በበኩላቸው፣ በማዕከሉ ሁሉም ምርት መኖሩን እና ዋጋውም ተመጣጣኝ በመሆኑ በቋሚነት ከማዕከሉ እንደሚሸምቱ ገልጸዋል።
መንግስት መሰል ማዕከላትን በመገንባት አምራቹ ያለምንም ውጣ ውረድ ከጓሮ የሚያመጣቸውን ምርቶች ወደ ገበያ በማቅረብ ከሸማቾች ጋር እንዲገናኝ በማድረጉ ተጠቃሚ መሆናቸውን በማዕከሉ በንግድ ሥራ ላይ ያገኘናቸው አምራች አብዲ ሚካኤል ተናግረዋል።
አቶ ፍቃዱ መለሰ የተባሉት አምራች በበኩላቸው፤ ምርቶች በቀጥታ ከገበሬው እንደሚመጡ እና ዋጋቸው ተመጣጣኝ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
መሰል የገበያ ማዕከላት የነዋሪውን ጥያቄ የፈቱ እና ለገበያ መረጋጋት ትልቅ አበርክቶ ያላቸው መሆኑንም አምራች እና ሸማቾቹ ጠቅሰዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ