በፓሪሱ የሙዚየም ስርቆት ተሳትፎ አድርገዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ተሰማ

You are currently viewing በፓሪሱ የሙዚየም ስርቆት ተሳትፎ አድርገዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ተሰማ

AMN – ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም

ባሳለፍነው ሳምንት በፈረንሳይ ፓሪስ ሉቬር ሙዚየም ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ውድ ጌጣጌጦችን ከሙዚየም ይዘው የተሰወሩ ዘራፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፈረንሳይ ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

በደቂቃዎች ውስጥ በጠራራ ጸሀይ ተፈጽሟል የተባለው ዝርፊያ ካሳለፍነው እሁድ ጀምሮ ሳምንቱን ሙሉ በአለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።

ዝርፊያው የተከናወነበት ፍጥነት እና ሙዚየሙ ለጉብኝት ክፍት በሆነበት ወቅት በድፍረት መፈጸሙ፤ ዘራፊዎቹ በሙዚየሙ ውስጥ የሚሰራ ሰው ድጋፍ አግኝተዋል የሚል ጥርጣሬን እንዲያጭር አድርጓል።

የፈረንሳይ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ቢሮ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በዝርፊያው ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ባሳለፍነው ቅዳሜ አመሻሽ ላይ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ቢሮው ባወጣው መግለጫ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ምን ያህል ሰዎችን እንደያዘ ይፋ ባያደርግም አንደኛው ተጠርጣሪ በፓሪስ በሚገኘው ቻርልስ ዲ ጋውል አየር ማረፊያ በኩል ከሀገር ሊወጣ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉን አመላክቷል።

የፈረንሳይ ጋዜጦች ፖሊስ ቅዳሜ አከናወንኩት ባለው እስር ምን ያህል ሰዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ባደረጉት ማጣራት፤ ከአራቱ ተጠርጣሪዎች መካከል ሁለቱ ብቻ መያዛቸውን ዘግበዋል።

ባሳለፍነው እሁድ በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በሚገኘው ሉቬር ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት በሆነ በደቂቃ ውስጥ ጭምብል ያጠለቁ ዘራፊዎች በ7 ደቂቃ ውስጥ እጅግ ውድ ታሪካዊ ጌጣጌጦችን ይዘው መሰወራቸው ይታወሳል።

በዝርፊያው ዘጠኝ ጌጣጌጦች የተሰረቁ ሲሆን ሁሉም በ19ኛው ክፍለ ዘመን የፈረንሳይ ንጉሣዊ ቤተሰቦች ይገለገሉባቸው የነበሩ 102 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ መሆናቸውን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review