መንግስት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር ያለውን ትብብር ያጠናክራል

You are currently viewing መንግስት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር ያለውን ትብብር ያጠናክራል

AMN ጥቅምት 17/2018

መንግስት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገንዘብ ሚኒስቴር ገለፀ።

የተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ፈንድና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እ.አ.አ ከ2025 እስከ 2030 በኢትዮጵያ በጋራ የሚተገበሩ የልማት መርሃ ግብሮች ስትራቴጂ ይፋ ተደርጓል።

መርሃ ግብሮቹ ተቋማዊ አቅምንና የሰው ሀብትን ማጠናከር፣ የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን ማሳደግ፣ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም ላይ ያተኮሩ ናቸው።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እንዳሉት፥ የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳዎችና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ሀገራዊ ጉዳዮች መሳካት የልማት አጋሮች እያደረጉ ያለው ድጋፍ ጉልህ ነው።

የተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ፈንድና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና በማኅበራዊ ልማት መስኮች አበረታች ስራዎችን ማከናወናቸውን አንስተዋል።

ሁለቱ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ይፋ ያደረጓቸው አዲስ መርሃ ግብሮች ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ያለንን የጋራ ጥረት የሚያሳይና ከኢትዮጵያ የልማት እቅዶችና ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር የተሰናሰሉ ናቸው ብለዋል።

የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትብብርና በመናበብ መስራት አስፈላጊ መሆኑን መንግስት ይገነዘባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለዚህም ከአጋር አካላት በጋራ በመስራት የስራ ድግግሞሽን እንዲቀንሱ ይሰራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለአምስት ዓመት በሚተገበረው የልማት መርሃ ግብር ተቋማትን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦችን የልማት እቅዷ አካል በማድረግ አካታች ብልፅግናን ለማሳካት እየተጋች መሆኗን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ፈንድ ተወካይ ኮፊ ኩዋሜ በበኩላቸው መርሃ ግብሮቹ በሰው ሀብት ልማት ያለንን ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በስርዓተ-ጾታ፣ ስነተዋልዶ ጤና፣ ሴቶችንና ወጣቶችን ማብቃት ላይ ያተኮሩና ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለመሆን እየሰራች ያለውን ተግባር የሚያጠናክሩ ስለመሆናቸውም ነው ያብራሩት።

የተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ፈንድ በመርሃ ግብሩ ከፌዴራልና ከክልል ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር እንደሚያጎለብት መጠቆማቸውን ተዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review