የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ የመጡት MAPARA A JAZZ የተባሉና የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ያላቸው ሁለት ግለሰቦች አዲስ አበባ ውስጥ አፈናና ድብደባ ተፈጽሞብናል ብለው በፌስ ቡክ ገፃቸው ያሰራጩት መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ማረጋገጡን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
እነዚህ ግለሰቦች ስራቸውን ጨርሰው በሠላም ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ አፈናና ድብደባ ተፈፅሞብናል ብለው በፌስ ቡክ ገፃቸው ያሰራጩትን መረጃ መሰረት በማድረግ ፖሊስ ተገቢውን የማጣራት ተግባር አከናውኗል።
ተፈፅሞብናል ስላሉት ወንጀል ለፖሊስ መረጃ ደርሶ እንደሆነ ለማረጋገጥ በክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና በፖሊስ ጣቢያዎች ተጠይቆ ምንም ዓይነት የቀረበ አቤቱታ አልተገኘም።

በፖሊስ ምርመራ የተሰባሰቡ የተንቀሳቃሽ ምስል፣ የፎቶና የድምጽ ማስረጃዎች እንዲሁም ከአዘጋጁ ቅሩንፉድ ኢንተርቴይመንት ጭምር እንደተረጋገጠው ግለሠቦቹ ይህን የሀሠት መረጃ የለቀቁት ብዙ ተከታዮችን ለማግኘት ሆን ብለው መሆኑን ተረጋግጧል።
ግለሰቦቹ አፈናና ድብደባ ተፈጽሞብናል ያሉት አርብ ጥቅምት 14 ቀን 2018 ዓ/ም ቢሆንም በማግስቱ ጥቅምት 15 በተጋበዙበት መድረክ ላይ ተገኝተው የሙዚቃ ስራቸውን ፍጹም ሠላማዊ በሆነ መንገድ አቅርበው ማጠናቀቃቸው እና በሠላም ወደመጡበት ሀገር መመለሳቸውን ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንዲሁም ከአዘጋጆቹ የተረጋገጠና ሲሆን የተሰራጨውም መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን ፖሊስ አረጋግጧል።
ከተማችን አዲስ አበባ በአስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ ላይ የምትገኝ ሲሆን የከተማዋን ብሎም የሀገሪቱን መልካም ገፅታ ለማጉደፍ የሚደረጉ መሠል እንቅስቃሴዎችን ህብረተሰቡ በንቃት ሊከታተልና የመረጃዎቹን ትክክለኛነት ሊያጤን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አሳስቧል።