በኢትዮጵያ የተሰራው ሪፎርም፣ ለብዙ ሀገራት ልምድ ሊሆን የሚችል ነው

You are currently viewing በኢትዮጵያ የተሰራው ሪፎርም፣ ለብዙ ሀገራት ልምድ ሊሆን የሚችል ነው

AMN – ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እያካሄደ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ አሁን ላይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው እድገት አፍንጫ ያለው ሰው በሽታ ያውቀዋል፣ ዓይን ያለው ሰው በአይኑ ያየዋል፣ ጆሮ ያለው ሰው ደግሞ በጆሮው ሰምቶ እና አሰላስሎ ይረዳዋል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተሰራው ሪፎርም፣ ለብዙ ሀገራት ልምድ ሊሆን የሚችል ከመሆኑም በላይ፣ የዓለም ባንክ፣ አይ ኤም ኤፍ እና ብዙ ሀገራት እንደ ልምድ ያነሱት የተሳካ ስራ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አንስተዋል።

ባለፈው አመት ብቻ ወደ ውጭ ከተላኩ ሸቀጦች 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአገልግሎትም 8 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማምጣት መቻሉን እና ይህም ትልቅ እምርታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የውጪ ምርቶቸን ተክቶ ማምረት በመቻሉ፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ወጪን ማዳን መቻሉንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ ውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር የገባው የገንዘብ መጠን 7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከውጭ በቀጥታ ኢንቨስትመንትም 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንም አንስተዋል።

በግብርናው ዘርፍ በተሰራው ስራም ከፍተኛ የምርት አቅርቦት በመገኘቱ፣ የገበያ መረጋጋቱ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ በምርት አቅርቦቱም የታረቀ እና የተስተካከለ እንዲሆን ረድቷል ነው ያሉት ።

ሸማቾችን እና አቅራቢዎችን ለማስተሳሰር በተሰራው ስራም የሰንበት ገበያዎች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ እነዚህ ገበያዎች ዋጋን ለማረጋጋት እና ህብረተሰቡ ሰፊ የገበያ አማራጮችን እንዲያገኝ አስችለዋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፡፡

ባለፈው ዓመት ለሴፍቲነት ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ድጎማ መደረጉን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች የኑሮ ጫና እንዲቋቋሙ ረድቷል ብለዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review