በሀገራችን የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መፃኢ እድል የሚወስኑ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ

You are currently viewing በሀገራችን የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መፃኢ እድል የሚወስኑ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ

AMN – ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም

በሀገራችን የተጀመሩ የጋዝ፣ የማዳበሪያ፣ የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ እና ሌሎችም ታላላቅ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መፃኢ እድል የሚወስኑ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እያካሄደ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ የዲዛይን፣ የአማካሪ መረጣና መሰል ቅድመ ዝግጅቶች የተጠናቀቁ መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ የልማት ተነሺዎችን አማራጭ ቤትና የተሻለ የኑሮ ዘይቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሰፊ ስራ በመሰራት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ 1ዐ ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግበት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዝና በአፍሪካ ትልቁ አየር ማረፊያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ በ24 ወራት የሚጠናቀቅ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እና የነዳጅ ማጣሪያ ለመገንባት ወደ ስራ መግባቷን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ይህም ኢትዮጵያ ከውጪ ታስገባ የነበረውን ማዳበሪያና ነዳጅ የሚያስቀር ሲሆን፣ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለተለያዩ ሥራዎች ግብአትነት ለመጠቀም ከፍተኛ አስዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

መንግስት የመኖሪያ ቤት ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ እና በ 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ወጪ በ6 አመታት ውስጥ ቤት ለመገንባት የሚሰሩ ፋብሪካዎችን ከውጪ በማስገባት ላይ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የሚገነቡት ቤቶች በ1 ወር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቁ ሲሆኑ፣ ለሙከራ በአዲስ አበባ ግንባታቸው በቅርቡ ይጀመራል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ይህም ሁሉም ሰው በቀላሉ የመኖሪያ ቤት ማግኘት ያስችላል፤ የኑሮ ጫናንም ይቀንሳል ነው ያሉት፡፡

በበረከት ጌታቸው‎

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review