ኢትዮጵያ ለመገንጠልም፤ ለመጠቅለልም አትመችም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰላም እና በፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ ለመገንጠልም ለመጠቅለልም አትመችም፤ በሀገር ውስጥ የቆየው የእርስ በእርስ ግጭት መቆም አለበት የሚለው ሀሳብ ቅቡልነት እንዳለው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ደካማ ሆና እንድትኖርና በሁለት እግሯ እንዳትቆም የሚሹ እና የሚሰሩ አካላት ሰላም እንዳይሰፍን በእጅ አዙር እንደሚሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ አንዳንዶችም የብሄራዊ ጥቅምን ካለመረዳት የተነሳ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ለጠላት ፍላጎትና ጥያቄ የተሰጡ አካላት መኖራቸውንም ተናግረዋል።

ይህም በኢትዮጵያ የተሟላ ሰላም ለማምጣት እክል መሆኑን ነው ያመላከቱት። ኢትዮጵያን በጦርነት ማሸነፍ እንደማይችሉ የተረዱ አካላት፣ በተላላኪዎች አማካኝነት ለመረበሽ እንደሚሞክሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ መንግስት አሁንም ከታጠቁ ሀይሎች ጋር በሰላም ጉዳይ ላይ ለመወያየትና በጋራ ለመስራትም ዝግጁ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
መንግስት ሰላም እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነት ከዚህ ቀደምም ከለውጡ ማግስት ማሳየቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወደ ሰላም የተመለሱትና ልብ የገዙት ሰክነው ለአገራቸው እየሰሩ ሲሆን፣ መላላክ የለመደው ደግሞ ወደ እዚያው መመለሱን ተናግረዋል፡፡
በሔለን ተስፋዬ