በሪፎርሙ ምክንያት ከ4 እስከ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የዕዳ ሽግሽግ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing በሪፎርሙ ምክንያት ከ4 እስከ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የዕዳ ሽግሽግ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN – ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ በሪፎርሙ ምክንያት ከ4 እስከ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የዕዳ ሽግሽግ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ኢኮኖሚን በተመለከተ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም የመንግስት ለውጥ ሲደረግ መንግስት የተዛባ ኢኮኖሚ እና ከፍተኛ ዕዳ መቀበሉን በመግለጽ፣ ያን ማረቅ አንዱ ዓላማው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ገቢ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ገቢን ለማሻሻል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እራሱን የቻለ ሪፎርም፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የስቲሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሰፋፊ ሥራዎች እንደተሰሩ እና አመርቂ ባይባልም ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ነው የገለጹት፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ገቢ መሻሻሉን በመጠቆም፣ በለውጡ ጊዜ 170 ቢሊየን ብር የነበረው የመንግስት ገቢ በዚህ ዓመት 1 ትሪሊየን ብር ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ሁለተኛው የወጪ ንግድን ማሻሻል ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍም በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡ ሪፎርም ሳይጀመር በፊት በ2016 በጀት ዓመት፣ ዓመቱን ሙሉ ወደ ውጭ የተላከውን መጠን በተያዘው በጀት ዓመት በ4 ወራት ብቻ ማከናወን መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

ይህም ማለት ሪፎርሙ የሚጨበጥ ውጤት ማምጣቱን አመላካች መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ትገኛለች የሚለውን ሀሳብ ትክክል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን በአፍሪካ አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሦስተኛ የሚባሉት ኢኮኖሚዎች በንፅፅር ሲታዩ ከኢትዮጵያ በብዙ እጥፍ ዕዳ እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም አንዱ ሀገር 300 ቢሊየን ዶላር ዕዳ፣ ሁለተኛው ሀገር 177 ቢሊየን ዶላር ዕዳ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ አካባቢ የሚገኙ ሀገራት እንኳን ከ78 ቢሊየን ዶላር በላይ ዕዳ አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ያለባት ዕዳ ከ23 ቢሊየን ዶላር እንደማይበልጥ ነው የገለጹት፡፡ በንፅፅር ሲታይ ያን ያክል አስደንጋጭ ባይሆንም የእኛ ሀገር ዕዳ መጥፎ የሆነው ብድር የወሰድንበት መንገድ ነው ብለዋል፡፡

አብዛኛው ብድር በአጭር ጊዜ ብዙ መክፈል የሚጠይቅ የብድር ሥርዓት ስለሆነ የመንግስት ጥያቄም የነበረው ያ የብድር ሁኔታ መሸጋሸግ አለበት የሚል መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በሪፎርሙ ምክንያትም ከ4 እስከ 4.5 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የዕዳ ሽግሽግ መደረጉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ታላቅ ድል የሪፎርሙ ውጤት ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review