አፍሪካ የመሰረተ ልማት ክፍተቷን ለመሙላት በየዓመቱ 130 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚገባት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
ሶስተኛው የአፍሪካ መሰረተ ልማት ፋይናንስ ጉባኤ ዛሬ በአንጎላ ሉዋንዳ ተጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የአንጎላ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ጆአኦ ሎሬንቾ፣ የአፍሪካ ሀገራትና መንግስታት መሪዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር አፍሪካ የመሰረተ ልማት ክፍተቷን ለመሙላት በየዓመቱ 130 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚገባት ገልጸዋል።
መሰረተ ልማት የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የጀርባ አጥንትና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ምሰሶ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ የመሰረተ ልማት ፕሮግራም(ፒዳ) በአህጉሪቱ 16ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ እና አራት ሺህ ኪሎ ሜትር የባቡር መንገድ ግንባታ መከናወኑን ጠቁመው 30 ሚሊዮን ዜጎች ኢነርጂ ተደራሽ ማድረጉን አመልክተዋል።
በሀገር በቀል የሀብት ማሰባሰብ፣ በአማራጭ ፋይናንስና በጠንካራ ዓለም አቀፍ አጋርነት አማካኝነት በቀጣይ ምዕራፍ የፕሮግራሙን ስኬታማነት የበለጠ ለማላቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የአፍሪካ የትስስር አጀንዳ ራዕይ ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቱ ስኬቶች በተግባር የሚረጋገጥበት መንገድ ጭምርም ነው ብለዋል።
የአንጎላ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ጆአኦ ሎሬንቾ ጉባኤው በአፍሪካ የሚገነቡ ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክቶች ሀብት የማሳባሰብና አፈጻጸም ደረጃ የሚገመገምበት መሆኑን አመልክተዋል።
ሶስተኛው የአፍሪካ መሰረተ ልማት ፋይናንስ ጉባኤ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚቆይ ኢዜአ ከህብረቱ የተገኘው መረጃ ያለክታል ።