ከ 2.7 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በ7 አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሊከናወን ነው

You are currently viewing ከ 2.7 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በ7 አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሊከናወን ነው

‎AMN- ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም

ከ2.72 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በሱማሌ፣ ብላቴ፣ በአሳሳ፣ በቦቆጂ፣ በላይኛው ወይጦ እና በላይኛው ኦሞ አካባቢ የከርሰ ምድር ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማከናወን ውል ስምምነት ተደርጓል።

ስምምነቱ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እየተተገበረ የሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት አካል መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ 2 ቢሊየን 723 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን፣ በውሉ መሰረት በ240 ቀናት እንደሚጠናቀቅ ሚኒስቴሩ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡ በስምምነት ፊርማው ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)፣ ፕሮጀክቱ እንደ ተቋም ትልቅ ስኬት መሆኑን አንስተዋል፡፡

የአካባቢውን ህብረተሰብ ከውሃ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በሚመልስ መልኩ ለመፍታት እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ጥራቱን ጠብቆ እንዲሰራና የማማከር ስራውን በሚገባ በማከናወን ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ስራው ለአካባቢው አርብቶአደር ማህበረሰብ ውሃ ለማቅረብ ታሳቢ ተደርጎ የተቀረፀው ፕሮጀክት፣ በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለበትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ በፕሮጀክቱ 49 የከርሰ ምድር ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ የሚከናወን ሲሆን፣ ከ500 ሜትር በላይ ጥልቀት እንደሚሸፍን ገልጸዋል፡፡

ከ8 ኮንትራክተሮች ጋር የተወሰደው የጉድጓድ ቁፋሮ ውል ለመጠጥ ውሃ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ያላትን የከርሰ ምድር ውሃ መጠን በማጥናትና በማወቅ ጉድጓዶችን መፈተሽ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ኮንትራቱን የፈረሙት አማካሪዎችና ኮንትራክተሮችም ሌት ተቀን በጥራትና በፍጥነት ሰርተው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review