በሰዓት 209 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ጃማይካን የመታው አውሎ ነፋስ ኩባ መድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሜሊሳ የሚል ስያሜ የተሰጠው አውሎ ንፋሱ፤ ባለንበት ጥቅምት ወር መጀመሪያ ከምዕራብ አፍሪካ የባህር ዳርቻ በመነሳት ወደ ደቡብ ካሪቢያን ባህር ማቅናቱን እና ማክሰኞ እለት ጃማይካን፤ ረቡዕ ደግሞ ኩባን መምታቱን ተዘግቧል፡፡
በዘመናዊ ታሪኳ አይታው የማታውቀውን አይነት ከባድ አውሎ ንፋስን ያስተናገደችው የካሪቢያን ሃገሯ ጃማይካ፤ ከፍተኛ የሆነ የሃይል መቋረጥ እና ጎርፍ ያስተናገደች ሲሆን በአደጋው በርካታ ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን የሃገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡
ዝናብ በቀላቀለው አውሎ ንፋስ በጃማይካ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል፡፡
በኩባ ከባድ ዝናብ ያስከተለው ይኸው አውሎ ንፋስ፤ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለቅድመ ጥንቃቄ አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሄዱ ምክንያት ሆኗል፡፡
አውሎ ንፋሱ ከኩባ ቀጥሎ ወደ ባሃማስ እና ቤርሙዳ ደሴት እንደሚያቀናም የአየር ትንበያ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
በሊያት ካሳሁን