ኢትዮጵያ እያካሄደች ባለዉ ሃገራዊ የምክክር ሂደት በርካቶች ከመሳተፋቸዉም በላይ አጀንዳዎቻቸዉን በመስጠት ላይ እንደሚገኙና ጫፍ የወጡ ሃሳቦች ጭምር እየተንጸባረቁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ በተካሀደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደች ካለዉ ሃገራዊ የምክክር ሂደት ጋር በተያያዘ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ እየተገባደደ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሃገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ ሃገራት ጭምር በርካቶች በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደቱ ላይ መሳተፋቸዉን እና ለምክክር ይበጃል ያሉትን አጀንዳ መስጠታቸዉን አንስተዋል፡፡

በለንደን ከተካሄደዉ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ሂደት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያዊያን ጋር ተቀላቅለዉ ሰልፍ በመዉጣት ምክክር አያስፈልግም የሚል ድምጽ ማሰማታቸዉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤርትራዊያኑ በኢትዮጵያ የዉስጥ ጉዳይ ከመግባት ይልቅ የሃገራቸዉን ዉስጣዊ ችግር በምክክር ቢፈቱ የተሻለ ይሆናል ብለዋል፡፡
በተለያዩ ክልሎች፤ ከተሞችና ዉጭ ሃገራት ጭምር በተካሄዱ አጀንዳ የማሰባሰብ የምክክር ሂደቶች በርካታ አጀንዳዎች መገኘታቸዉን እና ጫፍ የወጡ ሃሳቦች ጭምር እየተንጸባረቁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
አሁን ያለዉ ሂደት አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጀንዳ ተሰባስቦ ከተጠናቀቀ በኋላ ዉይይት እንደሚካሄድበት፤ አብዛኛዉ የተስማማበት አጀንዳ ለቀጠዩ ሂደት እንደሚያልፍ እና አብዛኛው ያልተስማማበት አጀንዳ ደግሞ በአሰራር ሂደቱ መሰረት የሚታይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሃገራዊ ምክክሩ ከሃገራዊ ምርጫዉ ጋር ምንም ትስስር የለዉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ሀገራዊ ምክክሩ ያለዉን ስርዓት የሚያጠናክር እንጂ የሚያፈርስ አይደለም ብለዋል፡፡
ሃገራዊ ምክክሩ ከምርጫ በፊትም ሆነ ከምርጫው በኋላ ቢጠናቀቅ ለሃገሪቱ ትልቅ ግብአት የሚገኝበት ይሆናል እንጂ በሃገራዊ ምርጫዉ የሚፈጥረዉ አንዳችም ተጽእኖ አይኖርም ብለዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ