የኮሪደር ልማት ገፀ በረከት የሆናቸው የከተማችን ሰፈሮች በነዋሪዎች አንደበት

You are currently viewing የኮሪደር ልማት ገፀ በረከት የሆናቸው የከተማችን ሰፈሮች በነዋሪዎች አንደበት

‎AMN – ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም

‎ከተሞችን ማዘመን፣ ለኑሮ ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፣ ገጽታን ማሻሻል እና ስማርት ሲቲን መፍጠር እንደሚገባ ይታመናል።

‎ለከተማ መስፋፋት፤ ለኑሮ ሁኔታ መሻሻል፣ የትራንስፖርት እና የመሠረተ ልማት ፍላጎቶችን ለመፍታት እንደ ኮሪደር ልማት ያሉ ኘሮጀክቶች አስፈላጊነት ከህዝብ አንደበት እየተሰማ ይገኛል። ሰው ተኮር የሆነው ይህ ልማት በምዕራፍ ተከፋፍሎ በጥራት እና በፍጥነት እየተሠራ ሲሆን አብዛኛው ተጠናቆ ለህዝብ ክፍት ተደርጓል።

‎ለህዝብ ክፍት ከተደረጉት መካከል የሳር ቤት፣ የጀርመን አደባባይ ጋርመንት ፉሪ አደባባይ የኮሪደር ልማት ይገኝበታል። ኤ ኤም ኤን በእነዚህ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።

ትውልድ እና እድገታቸው ሳር ቤት አከባቢ መሆኑን የገለፁት ‎‎አቶ ስሜነህ ተረፈ፤ በከተማዋ እየተሰሩ ባሉና በተሰሩ የመሰረተ ልማት እና መዝናኛ ስፍራዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን አመስግነዋል።

‎በተለይም የኮሪደር ልማቱ የመንገድ ላይ መብራቶችን ችግር በመቅረፉ ምንም አይነት የደህንነት ስጋት ሳይፈጥርባቸው እንዲንቀሳቀሱ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል። ታዳጊ ታሪኩ ዳዲ የ 5ኛ ክፍል ተማሪ ነው፤ በኮሪደር ልማት የተሰሩ የህፃናት መጫወቻ ቦታዎች በዕረፍት ጊዜ ለመዝናናት አመራጭ መሆናቸውን ነው የገለፀው። የመጫወቻ ቦታዎቹ አስደሳችና ለመኖሪያው ቅርብ መሆናቸው ከወንድምና እህቶቹ ጋር በጋራ ለመዝናናት አመቺ እንደሆነለት ገልጿል።

‎ወጣት ፋጡማ ዓሊ በዚሁ ቦታ ለመዝናናት ከመጡት መካከል አንዷ ናት። ቦታው ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁኔታ ጋር አይገናኝም፤ ስራዎቹ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ተደርጎ የተሰራ ነው ስትል አጫውታናለች፡፡

‎ለህዝብ ክፍት የተደረገው የአካባቢው ኮሪደር አረንጓዴ፣ ምቹ እና ነፋሻማ ነው ትላለች።

‎ከሳር ቤት ፣ ጀርመን አደባባይ ፣ጋርመንት ፉሪ አደባባይ ኮሪደር ልማት በመሰራቱ በተለይም የህፃናት መጫዎቹ ፣ ለታዳጊዎች እና ለወላጆች እፎይታን የሰጡ፤ ለትውልዱ የሚጠቅሙ መሆናቸውን የገለፁ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች፤ አካባቢው ከዚህ በፊት ከነበረው ቆሻሻ ዕይታ አሁን ላይ ንጹህ፣ ፅዱ እና ለአይንም ማራኪ ወደመሆን ተቀይሯል ይላሉ፡፡

‎በ 1ኛ እና በ2ኛ ዙር የኮሪደር ልማት ከተሰሩ መሰረተ ልማቶች መካከል 342 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ ፣ 185 ኪ.ሜ የተሽከርካሪ መንገድ ፣ 241 ኪ.ሜ የሳይክል መንገድ ይገኝበታል።

‎ዘመናዊ የመንገድ መብራቶች፣ በርካታ የህዝብ መገልገያ እና መዝናኛ ቦታዎች፣ በርካታ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች፣ 101 የህፃናት መጫወቻዎች፣ 155 የስፓርት ማዘውተሪያዎች፣ 153 ዘመናዊ ፓርኪንግ እና ተርሚናሎች እንዲሁም 210 የሕዝብ መፀዳጃዎች ተገንብተዉ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review