በእንግሊዝ ካራባኦ ካፕ የ4ኛ ዙር ጨዋታዎች ሊቨርፑል በክሪስታል ፓላስ ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።
የውጤት ማጣቱ የቀጠለው ሊቨርፑል በፓላስ 3ለ0 ተሸንፏል።ኢስማኤላ ሳር ሁለት እንዲሁም ያርሚ ፒኖ የፓላስ ግቦችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። የለንደኑ ክለብ በውድድር ዓመቱ ሊቨርፑልን ሦስት ጊዜ ገጥሞ ሁሉንም በድል ተወጥቷል።
የፊታችን ቅዳሜ በፕሪሚየር ሊጉ አስቶንቪላን ፣ ማክሰኞ ደግሞ በቻምፒየንስ ሊጉ ሪያል ማድሪድን የሚገጥሙት አርነ ስሎት በርካታ የዋናው ቡድን አባላትን አሳርፈው ለታዳጊዎች እድል ተሰጥተዋል። በጨዋታው ተቀይሮ የገባው ታዳጊ ተከላካይ አማራ ናሎ 79ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ወጥቷል።
በሌሎች ጨዋታዎች አርሰናል በሜዳው ኤምሬትስ ብራይተንን አስተናግዶ 2ለ0 አሸንፏል። ኢታን ዋኒዬሪ እና ቡካዮ ሳካ የማሸነፊያ ግቦቹን ከመረብ ማሳረፍ ችለዋል።
ከሜዳው ውጪ ወልቭስን የገጠመው ቼልሲ 4ለ3 በማሸነፍ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል። ማንችስተር ሲቲም ስዋንሲ ሲቲን 3ለ1 በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር መቀላቀል ችሏል።
በተመሳሳይ ኒውካስትል ዩናይትድ ቶተንሃምን አስተናግዶ 2ለ0 አሸንፏል። በሩብ ፍፃሜው አርሰናል ከ ክሪስታል ፓላስ ፣ ካርዲፍ ሲቲ ከ ቼልሲ ፣ ማንችስተር ሲቲ ከ ብሬንትፎርድ እንዲሁም ኒውካስትል ዩናይትድ ከ ፉልሃም ይጫወታሉ።
በሸዋንግዛው ግርማ