በተያዘው በጀት ዓመት ከ8.5 እስከ 9 ሚሊየን ሄክታር በሚጠጋ ማሳ ላይ ስንዴ ይመረታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምስራቅ ሸዋ ዞን የክረምት ስንዴ ምርት አሰባሰብ ሂደትን በመጎብኘት የበጋ ስንዴ ልማት ሥራን አስጀምረዋል። በጉብኝቱ ወቅት በሰጡት አስተያየትም፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ በክረምት ወራት 4.5 ሚሊየን የሚጠጋ ሄክታር መሬት በስንዴ መሸፈኑን የገለጹ ሲሆን፣ በበጋም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመት ከ8.5 እስከ 9 ሚሊየን ሄክታር በሚጠጋ ማሳ ላይ ስንዴ እንደሚመረት በመግለፅም፣ ከአምናው ምርት በእጅጉ የበለጠ እንደሚሆንም አመላክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምስራቅ ሸዋ ዞን ባደረጉት ጉብኝት፣ ከስንዴ በተጨማሪ የሙዝ፣ የፓፓያ እና የዓሣ ምርቶች ማየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ይህም ለጤና፣ ገንዘብና ሀብት ለማግኘት እንዲሁም በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል የሚያግዙ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የገጠር ሽግግርን ለማረጋገጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ150 ሺህ በላይ የውሃ ፓምፖች ወደ ስራ መግባታቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በ10 ሺህ የሚገመቱ ትራክተሮች እና 1 ሺህ ኮምባይነሮች ስራ ላይ መዋላቸውን ጠቁመዋል።
አሁንም በበሬ የሚያርሱ አርሶ አደሮች ቢኖሩም፣ ማሽን የማበራከቱ ጉዳይ እየጨመረ መጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፓምፕና ትራክተር ከውጭ ከማስገባት ባለፈ በሀገር ውስጥ ማቅረብ መጀመሩንም ተናግረዋል።
ፓፓያና ሙዝ ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑ ዝርያዎችን ከውጭ በማምጣት የምምረት ስራ እየተከናወነ እንደሆነና እነዚህን በምርምር በማሻሻል ከሄክታር የሚገኘውን ምርት የማሳደግ ስራ እንደሚከናወን አንስተዋል፡፡
ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በእጅጉ እንደሚያግዝ ነው ያመላከቱት።