የዐቃብያነ ሕግ የትብብር ፎረም ተለዋዋጭ በሆነው የአለም ሥርዓት ሀሳብ ለመለዋወጥ ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ሲሉ የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ ገለጹ

You are currently viewing የዐቃብያነ ሕግ የትብብር ፎረም ተለዋዋጭ በሆነው የአለም ሥርዓት ሀሳብ ለመለዋወጥ ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ሲሉ የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ ገለጹ

AMN ጥቅምት 19/2018

የቻይና-አፍሪካ የዐቃብያነ ሕግ የትብብር ፎረም ከምን ጊዜውም በላይ ተለዋዋጭ ሆኖ በመጣው የቴክኖሎጂ ሥነ-ምህዳር እና የባለብዙ ዋልታ የአለም ሥርዓት ፈተናዎች እና በመልካም አጋጣሚዎች ላይ ሀሳብ ለመለዋወጥ ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው ሲሉ የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያሥላሴ ገለጹ።

የቻይና-አፍሪካ የዐቃብያነ ሕግ የትብብር ፎረም በቻይና ጓንዶንግ ግዛት ጓንጁ ከተማ ዛሬ በይፋ ተከፍቷል።

በመድረኩ ንግግር የሰደረጉት የፍትሕ ሚኒስትሯ፥ የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም በአፍሪካ ሀገራት እና በቻይና መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ይበልጥ እያጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በተለይም በኢኮኖሚ እድገት እና ሁሉንም ወገን ያከበረ ፖለቲካዊ አጋርነትን እውን በማድረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣ የትብብር ሥርዓት መፈጠሩን ገልጸዋል።

የቻይና-አፍሪካ የዐቃብያነ ሕግ የትብብር ፎረም መካሄዱ ተለዋዋጭ በሆነው የአለም ሥርዓት ሀሳብ ለመለዋወጥ ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስትሯ በንግግራቸው፥ ዐቃቤ ሕግ ፍትሕን ለማስፈን እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

በቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም የድርጊት መርሀ-ግብር ላይ እንደተመላከተው የአፍሪካ ሀገራት እና ቻይና በሰላም እና መረጋጋት ዙሪያ በትብብር ለመስራት ባደረጉት ስምምነት መሰረት ፈተናዎችን ከምንጊዜውም በተጠናከረ የትብብር መንፈስ መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የፖለቲካ እና ሕግ ጉዳዮች ኮሚሽን ጸሐፊ ቼን ዌንኪንግ የአፍሪካ እና የቻይና የዐቃብያነ ሕግ ትብብር ፎረም በአፍሪካ ሀገራት እና በቻይና መካከል የሕግ የበላይነት መከበር ለአንድ ሀገር መዘመን የሚኖረውን ገንቢ ሚና በመረዳት ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በቀጣይም በአፍሪካ ሀገራት እና ቻይና የእርስ እርስ የልምድ ልውውጦችን በማድረግ በጋራ አብረው መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በፎረሙ ላይ ኢትዮጵያ፣ አልጄሪያ፣ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ግብጽ፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባቡዌ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review