የባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የማግኘት ብቻ ሳይሆን የደህንነት፣ የክብርና የህልውና ጉዳይ ነው

You are currently viewing የባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የማግኘት ብቻ ሳይሆን የደህንነት፣ የክብርና የህልውና ጉዳይ ነው

AMN – ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም

የባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የማግኘት ብቻ ሳይሆን የደህንነት፣ የክብርና የህልውና ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ካነሷቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል የባህር በር ጉዳይ አጽንኦት የሰጡበት ዋናው ጉዳይ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ በሰብዓዊ፣ በዲኘሎማሲ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ እና በዓለም አቀፍ ህግ ኢትዮጵያ ሀቅ እንዳላት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሠላም እና ደህንነት ተመራማሪ የሆኑት ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር)፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባነሱት የባህር በር ጉዳይ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በአለም ላይ ካሉት ሀገራት መካከል ብቸኛዋ ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር ኖሯት የባህር በር የሌላት ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን ገልፀው፣ ይህንን ዓለምም አፍሪካውያን ወንድሞችም በሚገባ የሚያውቁት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከ3ዐ የጦርነት ዓመታት በኋላ ኤርትራ ሀገር በሆነችበት ወቅት ኢትዮጵያ የባህር በር እንዴት እንዳጣች፣ በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግስት እንዲህ አይነት ውሳኔን የመወሰን ሥልጣን ነበረው ወይ የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት እንደሚነሱ ተመራማሪው ገልፀው፣ ይህንን ውሳኔ ለመወሰን የህዝብ ቅቡልነት ሊኖረው ይገባ ነበር ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን ኤርትራ ስትገነጠል የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ ይቻል እንደነበር በመግለፅ፣ የባህር በር ስለማጣቷ ግን የሚገልፅ ምንም አይነት ሰነድም አልተገኘም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጥቅም የማግኘት ብቻ ሳይሆን የደህንነት፣ የክብር እና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ጥያቄ ልክ እንዳልሆነ የሚያነሱ አካላት ትክክል አለመሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደፊት የህዝብ ቁጥሯ እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ በርካታ ወደቦች ሊያስፈልጋት እንደሚችል በመጠቆም፣ ኤርትራውያን ይህንን ሃቅ በመረዳት በሰላማዊ መንገድ ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር ሊቆሙ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review