ቦታዎችን ከህግ አግባብ ውጪ ሲጠቀሙ የተገኙ ባለይዞታዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

You are currently viewing ቦታዎችን ከህግ አግባብ ውጪ ሲጠቀሙ የተገኙ ባለይዞታዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

AMN – ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም

‎በመዲናዋ በሊዝ የተላለፉ ቦታዎች ከህግ አግባብ ውጪ ሲጠቀሙ የተገኙ ባለይዞታዎች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል ።

‎ቢሮው የተሻሻለው የከተማ ሊዝ አዋጅ 721/2004 ዓ.ም ተከትሎ በወጣው ደንብ ቁጥር 162/2016 መሰረት፣ መሬቱን ከወሰዱበት ዓላማ ውጪ ለሌላ አገልግሎት ሲጠቀሙ የተገኙ ባለይዞታዎች ላይ ፍተሻ በማድረግ የእርምት እርምጃ ወስዷል።

‎በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኮንን ተረፈ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም ‎የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ በበጀት ዓመቱ በሊዝ ውል መሬት የሰጣቸውን ይዞታዎች ያሉበትን ሁኔታ መቃኘቱን የገለጹት ኃላፊው፣ ከዚህ ውስጥ በህጉ መሰረት የአገልግሎት ለውጥ ያደረጉ ባለይዞታዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከሊዝ ውል ውጪ ወይም የህግ አግባብነት በሌለው መንገድ የመሬት አጠቃቀም ለውጥ ያደረጉ ባለይዞታዎች በተደረገው ክትትል መገኘታቸውን ኃላፊው ገልፀዋል።

‎ከህግ ውጭ የመሬት አጠቃቀም ለውጥ ያደረጉ ባለይዞታዎችን እንዲያስተካክሉ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን፣ አገልግሎት መቀየር የፈለጉትን ደግሞ በህጉ መሰረት እንዲቀይሩ መደረጉን አመላክተዋል።

‎በክትትሉ የተገኙ ውጤቶች በርካታ መሆናቸውን አስረድተው፣ ከተገኙት ውጤቶች መካከል የአሰራር ስርዓትን ማስፈን እና ፍትሀዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

በክትትሉ ለተለያዩ የልማት ስራዎች ሊውል የሚችል በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚሰበሰብ ሊሰወር የነበረ 9 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም የመኖሪያ ቤት የነበረውን ወደ ንግድ ወይም ወደ ሌሎች አገልግሎቶች ሲቀይሩ የመሬት አጠቃቀም ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚገባ ኃላፊው ገልፀዋል።

‎አዋጅ ቁጥር 721/2004፣ ደንብ ቁጥር 49/2004 እንዲሁም ይህንን ደንብ ለማስፈፀም የወጣውን መመሪያ በህግ የሚደግፉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

‎ከተጠቀሱት ህጎች በተጨማሪ ለመኖሪያ ቤት አገልግሎት የተወሰደ መሬትን ወደ ንግድ ለሚቀይር የመሬት አጠቃቀም ለውጥ ማድረጉ በደንብ ቁጥር 162/2016 ዓ.ም ላይ መደንገጉን ተናግረዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review