ሁለቱ የአለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች በመካከላቸው ያለውን የንግድ ጦርነት ለማርገብ ተስማሙ

You are currently viewing ሁለቱ የአለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች በመካከላቸው ያለውን የንግድ ጦርነት ለማርገብ ተስማሙ

AMN – ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም

ለቀናት በእስያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ሺ ዢንፒንግ ጋር በዛሬው ዕለት ተገናኝተዋል።

ከ2019 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙት ሁለቱ መሪዎች በመካከላቸው የሚኘውን የንግድ ጦርነት ረገብ ለማድረግ ተስማምተዋል።

ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት ላይ ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ አድርገው የነበረ ቢሆንም በኢኮኖሚ ተቀናቃናቸው ቻይና ላይ የጣሉት ታሪፍ ግን በመጠኑ ከፍተኛ እንደነበር ይታወሳል።

ቻይና በወሰደችው ተመሳሳይ እርምጃ ሁለቱ ሀገራት ከፍ ያለ ውጥረት ውስጥ ከመግባታቸው ባለፈ የታሪፍ ጭማሪው በአለም አቀፍ ኢኮኖሚ እና የንግድ እንቅስቃሴ ላይም ጫና አሳድሯል።

ሁለቱ መሪዎች በዛሬው ግንኙነታቸው ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት ትራምፕ፤ በቤጂንግ ላይ ተጥሎ የነበረውን 57 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ወደ 47 በመቶ ዝቅ ለማድረግ መወሰናቸውን አሳውቀዋል።

ከዚህ ባለፈም በብዛት መነሻውን ከቻይና እንዳደረገ የሚነገርለትን እና ለብዙ ሰዎች ህልፈት ምክንያት የሆነውን “ፌንትሌን” የተሰኘውን ሱስ አሲያዥ አደገኛ መድሀኒት ዝውውር ቁጥጥር ለማድረግ መስማማታቸውም ተገልጿል።

መሪዎቹ በደቡብ ኮሪያ ቡታን ውይይት ካደረጉ በኋላ ለመኪና ፣ አውሮፕላን እና ጦር መሳሪያ ምርት የሚያገለግሉ ልዩ ማዕድናትን ቻይና ለአሜሪካ ገበያ ማቅረቧን እንደምትቀጥል አስታውቃለች።

በሁለቱ የአለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ በኒውዮርክ እና በሌሎችም የአክሲዮን ገበያ ማዕከሎች መጠነኛ ዕድገት ታይቷል።

ሮይተርስ በዘገባው ስምምነቱ ከአክሲዮን ገበያ ባለፈ በአለም አቀፍ ኢኮኖሚ እና ምርት እንቅስቃሴ ላይ መሻሻል ሊታይ እንደሚችል አመላክቷል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review