የኢትዮጵያን የእንስሳት ሃብት ምርታማነት ለማዘመን የተተገበሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የዜጎችን የምግብ ዋስትናን እያረጋገጡ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
ከጥቅምት 20 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለሶስት ቀናት የሚቆይ የእንስሳት ሃብት ልማት፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን የሚያሳይ አውደ ርዕይና ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በአውደ ርዕይና ጉባኤው የተለያዩ ሀገራትን የወከሉ የግብርና ዘርፍ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የእንስሳት ሃብት ልማትና ተዋፅኦ ምርቶች፣ የዓሳና ንብ ማነብ ስራዎች ለዕይታ ቀርበዋል።
በዚሁ ወቅት በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አለማየሁ መኮንን (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን የእንስሳት ሃብት ለማዘመን የተተገበሩ ቴክኖሎጂዎች የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ ነው።
የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተግባራዊ የተደረጉ የእንስሳት ሃብት ልማት ስራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት እያሳደጉ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ለአብነትም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ምርታማነት የማሳደግ የዝርያ ማሻሻል ስራ በዜጎች ህይወት ላይ እመርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ አምባሳደር ክርስቲን ፕረን፤ የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት መርሃ ግብሮች የሀገሪቷን ዕድገት እየደገፉ ነው ብለዋል።
የኔዘርላንድስ መንግስትም የኢትዮጵያን የእንስሳት ሃብትና የግብርና ምርታማነት የእሴት ሰንሰለት ለማሻሻል ለሚከናወኑ ጥረቶች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን የእንስሳት ሃብት ምርታማነትን የሚያሻሽል የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የግብዓት አቅርቦትና የገበያ ትስስርን መፍጠር የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አውደ-ርዕዩ ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው ገልፀው፤ ምርታማነትን የሚሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን በኢትዮጵያ ገበያ ለማቅረብ ዕድል እንደፈጠረላቸውም ገልፀዋል፡፡