በ2018 በጀት በ1ኛው ሩብ አመት 284 ድርጅቶች እና 5 ሺ 512 ግለሰቦች በድምሩ 5 ሺ 796 በሚሆኑ ደንብ ተላልፈው በተገኙት አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታውቋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደተናገሩት፤ አንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ግለሰቦች ፍሳሽን ወደ ወንዞች በመልቀቅ የደንብ ጥሰቶችን ይፈፅማሉ ብለዋል።
ባለስልጣኑ ይህ እንዳይሆን በየጊዜው ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ቢሰጥም፣ ሴፍቲ ታንከራቸውን እና ትሪትመንት ፕላንታቸውን አዘጋጅተው ከመጠቀም ጋር ችግሮች በመኖራቸው አሁንም በወንዞች እና በወንዞች ዳርቻ ፍሳሽ የማስወገድ ተግባር እንደሚታዩ አስረድተዋል።
ከማስተማሩ ባሻገር ከድርጊታቸው በማይታቀቡት እና ደንብ በሚተላለፉት ላይ ባለስልጣኑ በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝም ምክትል ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
በዚህ መሰረት በተያዘው በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ አመት ብቻ 284 ድርጅቶች እና 5ሺ 512 ግለሰቦች በድምሩ 5ሺ 796 ደንብ በተላለፉ ላይ እርምጃ መወሰዱን ምክትል ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

በወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ አከባቢዎች 8ሺ በሚደርሱ ባለሙያዎች አማካኝነት በሶስት ፈረቃዎች በትኩረት የክትትል ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው አቶ ንጋቱ ዳኛቸው የገለፁት።
በተለይ በኮሪደር ልማት የለሙ አካባቢዎች ላይ የተፈጥሮ ሚዛኑን ጠብቆ እየሄደ ያለውን የወንዞች ፍሰት በአግባቡ እንዲሄድና በከተማዋ የመጣው ለውጥ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የደንብ ጥስትን በመከላከል ረገድ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲጎለብት በተለያዩ መድረኮች እና የተግባቦት አማራጮች በወጡት ደንቦች ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሰራቱንም አመላክተዋል፡፡
በዚህም መሰረት በ2018 በጀት ዓመት በመጀመሪዎቹ በሶስት ወራት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ 1.2 ሚሊዮን የሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉንም ነው የተናገሩት።
በዚህም የደንብ ጥሰት መተላለፍ ከ83 በመቶ በላይ መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ሌላው በደረቅ ቆሻሻ እና ፍሳሽ አወጋገድ እንዲሁም ህገ-ወጥ ማስታወቂያ፣ ህገ-ወጥ ግንባታ ዙሪያ የሚያጋጥሙ የደንብ ጥሰቶች የቀነሱ ቢሆንም፣ አሁንም በቅጣት ሰንጠረዥ ውስጥ ያሉ መሆናቸውን አመላክተዋል ።
በሔለን ተስፋዬ