የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን 17ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በአፍሪካ ኢኮኖሚክስ አዳራሽ ዛሬ አከናውኗል።
ፌዴሬሽኑ በ2017 በነበረው ክንውን የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች እንዲሁም የፖይለት ፕሮጀክቶች እድገት በጥሩ ጎን ተነስተዋል።
መንግስት ለስፖርቱ ትኩረት መስጠቱን የተናገሩት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ምክረ ሃሳብ አቅርበናል ብለዋል።
በሀገራችን እየተገነቡ ያሉት ስታዲየሞች 50 በመቶ ማለፋቸውን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ ደረጃቸውን የጠበቁ ማድረግ ላይ ተጨማሪ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይ የባህር ዳርና የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ በዘንድሮ በጀት አመት የመጠናቀቅ እድል እንዳለው ተናግረዋል።
ባለፈው አመት የሁለቱም ፆታ ብሄራዊ ብድኖች ከሜዳ ውጪ በመጫወታቸው ከ123 ሚሊዮን ብር በላይ ፌደሬሽኑ ወጪ ማውጣቱንም ገልፀዋል።
በተመዘገበው ውጤት ደስተኛ እንዳልሆኑ የገለፁት ፕሬዚዳንቱ ስፖርቱን በዘመናዊ መልኩ አደራጅቶ ዘላቂነት ያለው ውጤት ለማምጣት በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል።
በዮናስ ሞላ