የሀገሪቱን ሠላም ለማጽናት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች ውይይትን ባህል ሊያደርጉ ይገባል

You are currently viewing የሀገሪቱን ሠላም ለማጽናት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች ውይይትን ባህል ሊያደርጉ ይገባል
  • Post category:ፖለቲካ

AMN – ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም

የሀገሪቱን ሠላም ለማጽናት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ነፍጥ ያነገቡ ቡድኖች ውይይትን ባህል ሊያደርጉ እንደሚገባ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሠላምና ደህንነት ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) ገልፀዋል፡፡

ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ሀገራዊ ሠላም እንዲረጋገጥ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ነፍጥ ያነገቡ ቡድኖች በመወያየትና በመግባባት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት ባህል ሊያደርጉ ይገባል ነው ያሉት ፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት የሀገሪቱ የፖለቲካ ልምምድ ታሪክ የመጠፋፋት ነበር ያሉት ተመራማሪው፣ የሠላም እጦት ችግርን በውይይት የመፍታት ባህል ብዙ ርቀት ያልተሄደበት እንደነበር ነው ያወሱት፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ጥያቄዎቻቸውን በትጥቅ ትግል እናስመልሳለን የሚሉ ቡድኖች እና ሌሎችም የራሳቸው ርዕዮተ-ዓለም እና እይታ ያላቸው አካላት መኖራቸውን ጠቁመው፤ ነገር ግን ለሀገር እና ለህዝብ የሚበጀውን ብቻ በማድረግ ለሠላም መረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

በህገ-መንግስቱ መሰረት መንግስት በምርጫ ብቻ ወደ ስልጣን እንደሚመጣ መደንገጉን ያስረዱት ተመራማሪው፤ ይሁንና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ቡድኖች ሳይሳካላቸው ሲቀር ከውጭም ከውስጥም ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ አጀንዳዎችን ሲፈጥሩ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከመንግስት ጋር ልዩነት ያላቸው አካላት የማህበራዊ ድረ-ገፅን እና መሰል የመገናኛ ብዙሃንን ዘዴዎችን በመጠቀም ቅሬታቸው ተቋማዊ መልክ እንዲኖረው በማድረግ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመረበሽ እንደሚሰሩ ገልፀው፣ ይህም ሀገር እንዳትረጋጋ በማድረግ የወደፊት ራዕይን የሚያጨልም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የሀገሪቱን ሠላም ለማጽናት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና በትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ከመንግስት ጋር በሰከነ መንገድ ሃሳቦቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ችግሮችን በማጥበብና በመፍታት ውይይትን ባህል በማድረግ ሃገርን የሚያሻግር ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review