የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የተገልጋዩን ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
የ102 ዓመታት የካበተ ልምድ ያለው ሆስፒታሉ፤ በ2017 በጀት ዓመት 308 ሺህ ታካሚዎችን አስተናግዷል።
በቀን ከ844 በላይ ታካሚዎችን የሚያስተናግደው ሆስፒታሉ በተደራጀ መልኩ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም ከአገልግሎት ፈላጊው ብዛት አኳያ ግን አሁንም በተገልጋዮች በኩል የቅሬታ ድምጾች ይሰማሉ፡፡
አስተያየታቸውን ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የሰጡ የሆስፒታሉ ተገልጋዮች፤ በሆስፒታሉ የሚስተዋል የወረፋ መብዛት መኖሩንና በሀኪም የሚታዘዙ አንዳንድ መድሃኒቶችን በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ በሚገኘው መድሃኒት ቤት ለማግኘት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡
የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ፕሮቮስት ዶ/ር አንተነህ ምትኩ በበኩላቸው፣ ሆስፒታሉ የታካሚዎችን እንግልትና መጉላላት ለማስቀረት ከጠዋቱ 1 ሰዓት ጀምሮ የምዝገባና ካርድ የማውጣት ስራ ካከናወነ በኋላ 1፡30 ላይ ታካሚዎች ከዶክተሮቻቸው ጋር የሚገናኙበት አሰራር ተዘርግቷል ብለዋል፡፡
ዶ/ር አንተነህ አክለውም፣ የመድኃኒት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ የገበያ አማራጮችን በመጠቀም ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ አሁንም አልፎ አልፎ በግዥ መዘግየት ምክንያት አንዳንድ መድኃኒቶች በወቅቱ የማይቀርቡበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ሆስፒታሉ በላቦራቶሪ ግብዓት በተሻለ ሁኔታ የተደራጀ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር አንተነህ፣ የላቦራቶሪ ክፍሉ ምሳ ሰዓትን ጨምሮ ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት በመስጠት እየሰራ መሆኑንም አስምረውበታል።
ሆስፒታሉ የተደራጀ የመረጃ አያያዝና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን የተከተለ የጤና ተቋም መሆኑን ኤ ኤም ኤን በቅኝቱ ተመልክቷል።
በአለኸኝ አዘነ