ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ንጋት ሃይቅ የሚገኘውን የዓሳ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን እውቀት፣ጉልበትና ጥሪት ተገንብቶ ለስኬት የበቃ ታላቅ ፕሮጀክት ነው።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን ለኢትዮጵያ እድገትና ማንሰራራት አዲስ የታሪክ ምእራፍ የከፈተ የሀገር ሃብት መሆኑም ይታወቃል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ትሩፋት የሆነው ንጋት ሃይቅ ለዓሳ ምርትና ምርታማነት መጨመርና ለአካባቢው ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም እየሆነ መጥቷል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የተንጣለለውና ንጋት ሃይቅ በሚል የተሰየመው የውሃ ሃብት ከሌሎች ወንዞች ጋር ያለው ተፈጥሯዊ ግንኙነት ላቅ ያለ ነው።

በዚህም ሃይቁ በርካታ ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገር በውስጡ የያዘ መሆኑ ለዓሳ ሃብት ልማት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ንጋት ሐይቅ 15 ሺህ ቶን ዓሳ የማምረት አቅም እንዳለው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህም ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ የስራ እድል ይዞ መምጣት መቻሉን አብራርተዋል።
ከንጋት ሃይቅ የሚገኘውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ በዘላቂነት ለማረጋገጥ ግብርና ሚኒስቴር ጥናት ማካሔዱን ገልጸዋል።
በዚህም ሀይቁን ከተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች መከላከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የሀይቁን የደህንነት ስጋት ተጋላጭነት ቀድሞ መከላከል የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት ንጋት ሃይቅን ተከትሎ በዓሳ ማስገር ስራ ላይ የተሰማሩ 78 ማህበራት የተደራጁ ሲሆን 35ቱ በሙሉ አቅማቸው እየሰሩ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአጠቃላይ 866 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የማህበራቱ አባል በመሆን የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
 
								 
															 
 
							 
							