የባህር በር ጥያቄን የሀገር ህልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ አድርጎ ለተግባራዊነቱ የሚሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው ብለን እናምናለን ማለታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ተዘግቶባት መኖር አትችልም፤ለጎረቤቶቻችን መናገር የምንፈልገው ኢትዮጵያ ስታድግ ለቀጣናው ልማት ምንጭ ትሆናለች፤ የምንፈልገው በትብብር ማደግ ነው፤በመሆኑም የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው በማለት አጽዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ የኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራሮች የባህር በር ጥያቄ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከዓ ምድራዊ እውነታዎችን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የባህር በር የነበራት፣በቀጣናው ጂኦፖለቲካዊ እንቅስቃሴም ጉልህ ተሳትፎ የነበራት ሀገር መሆኗን አስታውሰው፥ ባለፉት 30 ዓመታት ያለባህር በር የቆየችበት ጊዜ የሚያስቆጭ መሆኑን አንስተዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ አቶ ታሪኩ ድምበሩ፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ አጀንዳ ሆኖ መምጣቱ ወሳኝና መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።
የባህር በር ጥያቄው የቅንጦት ሳይሆን የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑን በማመን የምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ የጉዳዩ አስፈላጊነትና ወቅታዊነት ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሶ ለተግባራዊነቱ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የባህር በር የሀገር ህልውና እና የትውልድ ጥያቄ በመሆኑ የትኛውም የፖለቲካ ተወናይ ይህንን እውነታ እና የሀገር ብሄራዊ ጥቅም የሚዘነጋው አይሆንም ያሉት የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ ለምላሹ የጋራ ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የባህር በር ለኢትዮጵያ ከድህነት የምትወጣበት፣በቀጣናው የዲፕሎማሲ ከፍታዋን የምታረጋግጥበት፣ንግዷን የምታሳልጥበት ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ምክር ቤቱ ይደገፋል ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ታፈሰ ናቸው።
የባህር በር ጉዳይን የአገር አጀንዳ እንዲሆን ላደረጉት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትልቅ ምስጋና እንደሚገባቸው አንስተው፥ ጥያቄው የኢትዮጵያን ህልውና ማረጋገጫ ዋና መሳሪያ ነው ብለዋል።
ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮችና መላው ህዝብ የባህር በር ጉዳይ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ በጋራ በመቆም ታሪካዊ ስራ መስራት አለበት ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
በክልሉ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች አባል የሆኑበት የጋራ ምክር ቤቱ፥ የባህር በር ጥያቄን የሀገር ህልውና እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ አድርጎ የሚወስደው መሆኑንና ለምላሹም የሚሰራ መሆኑን አረጋግጧል።
 
								 
															 
 
							 
							