ተደብቀው ከሚኖሩበት የድንጋይ ካብ ውስጥ እየወጡ በተለያዩ ግለሰቦች ላይ የውንብድና ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ከመኖሪያ አካባቢ ራቅ ብሎ በሚገኝ ቁጥቋጦ ውስጥ የድንጋይ ካብ ሰርተው በላስቲክ ከልለው ተደብቀው ሲኖሩ የነበሩ መሆናቸውን መመሪያው ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል።
ከግል ተበዳዮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አፍሬም ዋለልኝ የተባሉ ግለሰብ የውንብድና ወንጀል የተፈፀመባቸው ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ/ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ገደማ ነው።
ተጠርጣሪ አቡሽ አረጋ እና ማቲዮስ መንጌ የግል ተበዳዩ በዕለቱ በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 9 መገናኛ ተርሚናል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲንቀሳቀሱ ተከትለው በተመሳሳይ የወንጀል አፈፃፀም ሞባይል ስልካቸውን ከወሰዱባቸው በኋላ ሊያመልጡ ሲሞክሩ ፖሊስ ባደረገው ጥረት እና በህብረተሰቡ ትብብር እጅ ከፍንጅ መያዛቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ከተያዙ በኋላ የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የምርመራ እና የክትትል ቡድን በማቋቋም ባከናወነው ምርመራ የማስፋት ተግባር እና ባካሄደው ያልተቋረጠ ክትትል አባሪ ተባባሪ በመሆን ተመሳሳይ ወንጀል የፈፀሙ ጌቱ አበራ እና ባትሪ ባዛ የተባሉ ተጨማሪ ሁለት ግብራበሮቻቸውን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
መምያው እንደገለፀው በእነዚህ አራት ተጠርጣሪዎች ላይ የምርመራው ሂደት ተጠናክሮ በመቀጠሉ በጥቅምት ወር ውስጥ በተለያዩ ቀናት በክፍለ ከተማው የተለያዩ አካባቢዎች በሌሎች ሁለት ግለሰቦች ላይ ተመሳሳይ ወንጀል በመፈፀም ሞባይል ስልክ ቀምተው እንደተሰወሩ ማረጋገጥ ተችሏል።
የውንብድና ወንጀሉን ሲፈፅሙ የቆዩት አራቱ ተጠርጣሪዎች ወንጀል ከመፈፀማቸው በፊትም ሆነ ወንጀል ከፈፀሙ በኋላ የሚደበቁበትን የድንጋይ ካብ ለፖሊስ መርተው ያሳዩ ሲሆን ኑሮአቸውን በዚያ ካብ ውስጥ አድርገው እንደቆዩም በሰጡት ቃል መግለፃቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
ፖሊስ ከግል ተበዳዮቹ የተወሰዱ ሞባይል ስልኮችን ከተሸጡበት በምሪት ያስመለሰ ሲሆን በወንጀል የተገኙትን ስልኮች ገዝቷል የተባለውን ተጠርጣሪም በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ኅብረተሰቡ ወንጀል ፈፃሚዎችን አንገት ለአንገት ተናንቆ ከመያዝ ጀምሮ ለፀጥታ አካሉ ጥቆማ በመስጠት የከተማዋን ሰላም በዘላቂነት ለማፅናት የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክቱን ያስተላለፈ ሲሆን፤ በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ንብረታቸው የተወሰደባቸው ግለሰቦች የካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በአካል በመቅረብ ተጨማሪ መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
 
								 
															 
