አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሃይማኖት ተቋማት ሚና መጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሃይማኖት ተቋማት ሚና መጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

AMN ጥቅምት 21/2018

አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሃይማኖት ተቋማት እየተወጡ ያለውን ሚና ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀኃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ህብረት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ መክሯል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሃይማኖት ተቋማት ሚና መጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል።

”ያለ ሰላም መኖር አንችልም ሰላም ለሰው ልጆች የመጀመሪያውና ተቀዳሚ የህልውና አጀንዳ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ሀገር አቀፍ ኩነቱ የሃይማኖት ተቋማቱ ለሰላም፣ ለልማት እና ለአንድነት እንዲሁም ለሰላም እሴቶች መፅናት እያደረጉት ያለው ተግባር እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትልና የሰላም እሴት ግንባታና ብዝሃነት አያያዝ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በቀለ ሎኮርማ በበኩላቸው ክልሉን የሰላም ተምሳሌት ለማድረግ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም በሁሉም የክልሉ አካባቢ ህብረተሰቡ በተረጋጋ ሁኔታ የዕለት ተዕለት ተግባሩን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ክልሉ ይህን ታሪካዊ ጉባኤ ለማስተናገድ በመመረጡ መደሰታቸውን ጠቅሰው፤ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ጋሞ አካባቢ አስተማማኝ ሰላም ለመኖሩ የሚመክሩ አባቶችና የሚሰሙ ልጆች በመኖራቸው መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ተወካይና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ መስከረም ዛፉ ናቸው።

በከተማዋ የሚካሄደው 5ኛው ሀገር አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን ከህዝብ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ገበየሁ ፃራ በበኩላቸው ሰላም ለሁሉም መሠረት በመሆኑ በአካባቢው ያለው የሰላም ፀጋ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በጉባኤውም ሀገር አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ሲደረጉ የነበሩ ዝግጅቶች መጠናቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ህብረት የሚዘጋጀው 5ኛው ሀገር አቀፍ ጉባኤ በመጪው ህዳር ወር በአርባ ምንጭ ከተማ ይካሄዳል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review