በቀዳማይ ልጅነት ላይ የሚሰራው ስራ፣ የተሻለችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት የሚያስችል አርአያነት ያለዉ ፕሮግራም ነው

You are currently viewing በቀዳማይ ልጅነት ላይ የሚሰራው ስራ፣ የተሻለችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት የሚያስችል አርአያነት ያለዉ ፕሮግራም ነው

AMN – ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ከተማ የጀመረችው ፈጣን እድገት ዘለቄታ እንዲኖረው የነገ ትውልድን መሰረት ያደረጉ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች፡፡

ከእነዚህ ተግባራት መካከል የቀዳማዊ ልጅነት ፕሮግራም በዋናነት ይጠቀሳል፡፡

ይህ ፕሮግራም ህፃናት በእናታቸው ማህፀን እያሉ ጀምሮ እስከ ስድስት አመታት ድረስ በአካል እና በስነ-አእምሮ የበለፀጉ ይሆኑ ዘንድ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ወይዘሮ ዘሪቱ አያሌው የቀዳማዊ ልጅነት ፕሮግራም ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ከሆንኩ በኋላ የወለድኳት ልጅ ጤናማና ንቁ ነች ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል ፡፡

ሌላኛዋ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ወይዘሮ ይደነቅ አመሸህም የወይዘሮ ዘሪቱን ሀሳብ ተጋርተው፣ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ ከመሆኔ በፊት ያገኘሁትን ነገር ብቻ ነበር የምመገበው፣ አሁን ግን የተመጣጠነ ምግብ እያገኘሁ ነው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት የስትራቴጂክ ፕሮግራሞች ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ሀላፊ እሸትአየሁ ክንፈ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወነ ያለው የህፃናት የምገባ ድጋፍ ፕሮጀክት ሀገርና ትውልድን የመገንባት ሂደት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

80 ከመቶው የሚሆነው የሰው ልጅ አእምሮ የሚገነባው በመጀመሪያዎቹ 1ሺህ ቀናት ወይም ከ3 እስከ 4 አመታት ባሉት ጊዚያት ውስጥ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሀላፊ ወይዘሮ እመቤት ተስፋዬ በበኩላቸው፣ አሁን ላይ ከተማ አስተዳደሩ በቀዳማዊ ልጅነት ፕሮግራም በነገው ትውልድ ግንባታ ላይ አሻራውን እያስቀመጠ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በአዲስ አበባ ከተማ በ1.3 ሚሊዮን ህፃናት ላይ የሚሰራው የቀዳማይ ልጅነት ስራ ከ10 እና ከ15 አመታት በኋላ የተሻለችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት የሚያስችል ትልቅ ፕሮግራም መሆኑንም እሸትአየሁ ክንፈ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በመጀመሪያዎቹ ሶስት አመታት በተከናወነው የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ እጅ አጠሮች ድጋፍ እንዳገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ለቀጣይ 3 አመታት የሚቆየው የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም እንደተጀመረም ተመላክቷል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review