የንግዱ ማሕበረሰብ ሰላምን ከማስጠበቅ ረገድ ያለዉ ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing የንግዱ ማሕበረሰብ ሰላምን ከማስጠበቅ ረገድ ያለዉ ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ

AMN-ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም

የንግዱ ማሕበረሰብ ሰላምን ከማስጠበቅ ረገድ ያለዉ ሚና የላቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፤ “ንግድ ለሀገር ሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ኃሳብ ከባላ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።

በመርኃ ግብሩም የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሓራ መሓመድ ፤ ምክር ቤቱ፣ መንግስት እና የንግዱ ማሕበረሰብ በትብብር እንዲሰሩ ለማድረግ ድልድይ ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የምክክር መርሓግብሩም፤ የንግዱ ማሕበረሰብ ፤ ለሰላም ያለውን ግንዛቤ ለማስፋት ያግዘዋልም ብለዋል።

የሰላም ግንባታ ከአከባቢ ይጀምራል ያሉት ፤ ወ/ሮ ዛሓራ መሓመድ ፣ ሰላምን ለማግኘት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

በሌላ መልኩ፣ ሰላም የአንድ ሀገር የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ መሆኑን ያነሱት የኢትዮጵያ የሓይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሓፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ፤ የንግዱ ማሕበረሰብም ይህንኑ ሰላም በማስጠበቅ በኩል ፤ የራሱን አበርክቶ ማሳረፍ እንደሚገባውም አንስተዋል።

ቀሲስ ታጋይ ፣ ያለሰላም መስራትም ሆነ ከቦታ ቦታ በነጻነት መዘዋወር እንደማይቻል ገልጸው ሰላም ለንግድ ስራ መሳለጥ እንዲሁም ንግድም ለሰላም ስራ አበርክቶው ከፍ ያለ መሆኑን አመላክተዋል።

ለዚህም የንግዱ ማሕበረሰብ ለሰላም ትኩረት በመስጠት በሰላም ላይ ከሚሰሩ እንደ የኢትዮጵያ የሓይማኖት ተቋማት ጉባኤ ካሉ አጋር አካላት ጋራ በመተባበር በሰላም ግንባታ ስራው ላይ በስፋት ሊሳተፉ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

የንግዱ ማሕበረሰብ ከአሁን በፊት የሀገርን ችግር ለመፍታት የራሱን ሚና ሲወጣ መሰንበቱን ያነሱት የምክክሩ ተሳታፊዎችም በቀጣይም የሀገርን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል ።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review