ኢትዮጵያ

You are currently viewing ኢትዮጵያ
  • የባህር በሯን ያጣችበት መንገድ ህጋዊ መሠረት የለውም ተብሏል
  • መልሳ ለማግኘት ከመልክዓ ምድራዊ ቅርበቱና ታሪካዊ መሠረቱ እንደሚፈቅድላት ተጠቁሟል
  • ወደብ አልባ መሆን የአንድ ሀገር የውጭ ንግድ መጠንን እስከ 43 በመቶ ሊቀንሰው እንደሚችል ተመላክቷል

ኢትዮጵያ ረጅም እድሜ ያስቆጠረች ሀገር እንደመሆኗ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች። በታሪኳ የከፍታም ሆነ የዝቅታ ዘመናት እንደነበሯት ታሪካዊ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡ በአክሱማይት ስርወ መንግስት ዘመን በዓለም ላይ ከነበሩ አራቱ ኃያላን ሀገራት መካከል አንዷ እንደነበረች ኤድመንድ ጄ. ኬለር የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስትና ፖለቲካዊ ህልውና ቀጣይነት ሁኔታ አስመልክተው (The Politics of State Survival: Continuity and Change in Ethiopian Foreign Polic) በሚል ርዕስ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1987 ያሳተሙት ጥናታዊ ፅሑፍ ያስነብባል። ሀገሪቷ በዘመናት ሂደት ደጋግመው በገጠሟት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ሳቢያ ኢኮኖሚዋ ተዳክሞ የድህነት ምሳሌ ተደርጋም ታውቃለች፡፡

የውስጥ ሽኩቻዎች እና የውጭ ወረራዎች ክፉኛ ያጎሳቆሏት ሀገር ናት ኢትዮጵያ። ከውስጥ በዘመነ መሳፍንት፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት እና በሌሎች ጊዜያትም የገጠሟት ሁኔታዎች የሚታወሱ ናቸው፡፡ ከውጭ ደግሞ የግብፅ፣ የጣሊያን፣ የሱዳን፣ የሶማሊያን ወረራዎች መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሀገራት ግዛትን የማስፋፋትና የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት የመቆጣጠር ዓላማ አንግበው ተደጋጋሚ ትንኮሳዎችን አድርገውባታል፡፡ ቀደምት አያቶቻችን በተባበረ ክንድ የእነዚህን ሀገራት ትንኮሳዎችን እና ወረራዎችን ቀልብሰዋል። ሆኖም እነዚህ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ተደማምረው በርካታ ኪሳራዎችን በሀገር ላይ አስከትለዋል። ለአብነትም ሀገሪቷን የባህር በር አልባ አድርገዋታል፡፡

ኢትዮጵያ በጥንት በአክሱም ዘመነ መንግስትና ከዚያ በኋላም የነበሩ ስልጣኔዎች መሰረታቸው ከባህር ጋር የተቆራኘ ነው። ባህር ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምንጭ፣ የህልውና መጠበቂያ አቅም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም የፖለቲካ ሚዛን ማስጠበቂያ እንዲሁም ከውጭ ዓለም ጋር ለሚደረጉ የንግድ ልውውጥ ማሳለጫ በመሆን ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ኢትዮጵያ ከባህር በር እየራቀች በመጣች ቁጥር የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲና ራስን የመጠበቅ አቅሟ እየተዳከመ እንደመጣ የታሪክ ባለሙያዎች ያሳያሉ፡፡

በቅርቡ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት በአሜሪካ ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ እና በሀገር ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ሆነው የሰሩት አየለ በከሬ (ፕ/ር)፣ ባህር ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ አካል እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

አየለ በከሬ (ፕ/ር) በዓለም ላይ ዋነኛው የንግድ ልውውጥ መስመር ባህር ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የባህር በር በነበራት ጊዜ በስልጣኔና እድገት ወደፊት ሄዳ እንደነበር አውስተው፣ ከውጭ የሚያስፈልጋትን ዕቃዎች የምታስገባውና የምታስወጣባቸው አማራጭ ወደቦች በብዛት እንደነበሯት ጠቁመዋል፡፡ ከእነዚህም አዱሊስ፣ ዘይላ፣ በርበራ፣ ምፅዋና አሰብ እንደሚጠቀሱ ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በገጠማት የውጭ ወራሪዎች ጥቃት እና የሀገር ውስጥ የባንዳ ክህደት ሳቢያ በጊዜ ሂደት ወደቦቿን አንድ በአንድ እያጣች መጥታለች፤ በ1983 የመጨረሻው ክህደት ተፈፅሞባታል፤ በጫካ ህግ አንጡራ ሀብቷን ለማጣት ተገድዳለች፡፡ ለ30 ዓመታትም ይህን ጉዳይ ማንሳት እንደ ነውር ሆኖ ይቆጠር ነበር፤ ይህን አይነኬ ሆኖ የቆየ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት “ከጠብታ ውሃ እስከ ባህር ውሃ” በተሰኘው መድረክ አነሱ፤ ይህም የባህር በር ጉዳይ ዳግም እንዲነሳ እና ዜጎች ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን እንዲረዱ አድርጓል፡፡

ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ተገቢነት በጎደለው መንገድ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ከእጇ የወጣውን የባህር በር ባለቤትነት መልሳ ለማግኘት በሰላማዊ መንገድ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች። ጥረቷ መልካም ውጤት እያስገኘላት ስለመሆኑም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ለመሆኑ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን ያጣችበት ሂደት ከዓለም አቀፍ ህግ አንፃር እንዴት ይታያል? ከታሪካዊ ባለቤትነት እና መልክዓ ምድራዊ ቅርበት አንፃርስ መልሳ የማግኘት ዕድሏ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን አንስቶ ማብራራት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነቷን ያጣችበት ሂደት ግልፅ አለመሆኑ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ይህን ጉዳይ አንስተው አብራርተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም፣ የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ድንበርተኝነት ያሳጣው ውሳኔ በማን እንደተወሰነ የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃ አለመገኘቱን ጠቅሰው፣ ውሳኔው ሕጋዊ እንዳልሆነ አመላክተዋል፡፡

ታድያ እንዲህ ያለው ጉዳይ ከህግ አግባብ እንዴት ይታያል ያልናቸው የህግ ባለሙያው አቶ ኪያ ፀጋዬ፣ በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግስት እንደመሆኑ የባህር በርን በሚያህል ጂኦ እስትራቲካዊ ጉዳይ ላይ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የለውም፡፡ ስለዚህ ውሳኔው ህጋዊ መሠረት የለውም በማለት ጉዳዩን ማብራራት ጀምረዋል፡፡

የህግ ባለሙያው በማብራሪያቸው፣ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ለማሳተለፍ የሚችል ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ባልተመሰረተበት ሁኔታ ነው ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያጣችው፤ ተቀባዩም ሆነ ሰጪው ከጫካ የመጡ የጋራ ዓላማ የነበራቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ውግንና ቢኖራቸው ኖሮ በሺህ ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠር ርዝመት ያለው የባህር በር ያላትን ሀገር በአንድ ጀንበር ዝግ አያደርጓትም ነበር፡፡ ስለዚህ ህዝብ ተወያይቶ ያልደረሰበት ስምምነት እና በህዝብ የተመረጠ መንግስት በሌለበት የተላለፈ ውሳኔ በመሆኑ ህጋዊ መሠረት ያሳጣዋል ብለዋል፡፡

የባር በሩ የሄደበት መንገድ ቀርቶ ኤርትራ ራሷም የተገነጠለችበት መንገድ ሲፈተሽ ህጋዊ መሰረት የለውም ያሉት የህግ ባለሙያው፣ ሁኔታው ከድርጊቱ ጀርባ አንዳች ድብቅ ዓላማ መኖሩን ጠቋሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በር አልባ የማድረግ ደባ ነው የተፈፀመው፡፡ ምክንያቱም በጉዳዩ ውስጥ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እጅ አለበት ሲሉም አክለዋል፡፡

ለዚህም እንደማስረጃ ያቀረቡት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ያሳለፉት በትጥቅ ትግል ላይ የቆዩ አካላት ሲሆኑ ኤርትራ በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ውስጥ ነች ብለው የሚያስቡ  ከመሆናቸውም በላይ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ከሆነችው ግብፅ ጋር እጅና ጓንት ሆነው ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸውን ነው፡፡

የኢትዮጵያን የባህር በር የተወሰደበት ሂደት የተሳሳተና ደባ የተሞላበት መሆኑ አሁን ለማስመለስ እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ ህጋዊ አቅም እንደሚሰጥ የህግ ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በሯን መልሳ ለማግኘት ጂኦግራፊያዊ ቅርበቱ፣ ታሪካዊ መሠረቱ እና ዓለም አቀፍ ህጎች እንደሚፈቅዱላት ገልፀዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1994 “የተባበሩት መንግስታት የባህር ህግ ስምምነት” (United Nations Convention on the Law of the Sea) የተሰኘ የባህር ሕግን ስራ ላይ አውሏል። ይህ ሕግ በ168 ሀገራት የተፈረመ ነው። ይህም በጣም ተቀባይነት ካላቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንዱ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባህር ሕግ አንቀጽ 69 ንዑስ አንቀጽ 1 እስከ 5 የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባህር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ በዚሁ ሕግ በአንቀጽ 125 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደተቀመጠው የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ያለውን ባህር የመጠቀም እና የመሸጋገር ዓለም አቀፍ መብት እንዳላቸውም በጉልህ ሰፍሯል፡፡

ታዲያ ይህ መብት የባህር በር በሌለው ሀገር፣ የባህር በር ባለቤት በሆነው ሀገር እና በቀጣናው መካከል በሚደረግ ስምምነት ሊፈጸም እንደሚገባም በንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ተቀምጧል፡፡ አንቀጽ 27 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ደግሞ እነዚህ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በሰምምነት ከተደረገ የተለየ የአገልግሎት ክፍያ ከሌለ በስተቀር ለተገለገሉበት ባህር ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁም መደንገጉን የህግ ባለሙያው አቶ ኪያ ፀጋዬ ገልፀዋል፡፡

በዓለም ላይ ካሉ 195 ሀገራት መካከል 44 ሀገራት ወደ ባህር መውጫ በር የላቸውም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 32ቱ ከበድ ያሉ ፈተናዎች ያሉባቸው አዳጊ ሀገራት መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም መረጃ ያመላክታል። ኢትዮጵያ የባህር በሯን በግፍ ከተነጠቀችበት ጊዜ ጀምሮ ለበርካታ ውስብስብ ችግሮች ተዳርጋ ቆይታለች። ከውጭ የምታስገባው እቃዎች ሁሉ ተፈትሸው እንዲያልፉ ስለምትገደድ የደህንነት ጉዳይ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ድህነትን ለማሸነፍ የሚደረገው ጥረትም ተጠባቂውን ውጤት ሳያስገኝላት ቀርቷል፤ ምክንያቱም የባህር በር እጦት በጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ላይ ቀላል ያልሆነ ተፅዕኖ አለውና፡፡ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማርያም ‘አሰብ የማን ናት?’ በሚለው መጽሐፋቸው ይህን ጉዳይ በበቂ ደረጃ አብራርተውታል፡፡

ወደብ ያለው ሀገር ኢኮኖሚውን በእጥፍ ለማሳደግ 24 ዓመታት እንደሚፈጅበት የሚያትተው የዶክተር ያዕቆብ መፅሐፍ፣ ወደብ አልባው ሀገር ኢኮኖሚውን በእጥፍ ለማሳደግ 36 ዓመታት እንደሚወስድበት አብራርተዋል፡፡ ወደብ አልባ መሆን ብቻ የአንድ ሀገር የውጭ ንግድ መጠንን ከ33 በመቶ እስከ 43 በመቶ ሊቀንሰው እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡

ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይዞ የባህር በር የሌላት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች ያሉት የህግ ባለሙያው፣ “በዚያ ላይ የነበራትን ነው ያጣችው፡፡ አሁን ላይ የባህር በር የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የዓለም ማህበረሰብ እና ጎረቤት ሀገራት ይህን ጉዳይ በቅጡ አጢነውት ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡን ይገባል፡፡ አለበለዚያ ይዞት የሚመጣው ጦስ ለሁሉም ይተርፋል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባህር በርን መጠየቅ ነውርና ትክክል ያልሆነ አድርጎ የሚመለከት ትርክት እንዳለ ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ ባህር እንደሚያስፈልጋት እና ከኤርትራ ጋር ሰላም በተፈጠረበት ወቅት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በሚሊኒየም አዳራሽ ማንሳታቸውን ተናግረዋል፡፡ ወደ ኤርትራ በተጓዙበት ወቅትም ወደብ ዋነኛ ጉዳይ እንደነበር አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘቷ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን አንስተው፣ ቅድሚያ የምንሰጠውም ሰላም እና ንግግር ስለሆነ ሀገራት መፍትሔ እንዲያመጡ ጥሪ አቅርበዋል። ማንም ፈለገም አልፈለገም ኢትዮጵያ ተዘግታ እንደማትኖር እርግጠኛ ነኝ ብለው፣ ትልቅ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ስታድግ ሌሎችን የምታግዝ እንጂ ስጋት እንደማትሆን አረጋግጠዋል።

በተካልኝ አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review