መገናኛ ብዙሃን በአንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወትና እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡ መገናኛ ብዙሃን ህብረተሰብን በማስተማርና በማነፅ፣ የመንግስትን የልማት ትልሞች በማሳወቅ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና መፍትሔዎችን በማመላከት፣ በመንግስትና ህዝብ መካከል ድልድይ በመሆን አይተኬ ሚና እንደሚጫወቱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በየጊዜው ተደራሽነቱን እያሰፋ፣ የነዋሪዎችን ፍላጎት ለማርካት እየተጋ የሚገኘው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም ለህብረተሰቡ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮችና ቋንቋዎች ወቅታዊ፣ የህዝብን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ የሚያመላክቱ፣ አስተማሪና አዝናኝ መረጃዎችን እያደረሰ ይገኛል፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሜትሮፖሊታን ሚዲያ እንደመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ፍላጎት በማርካት፣ ተወዳዳሪና ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን በይዘት ፈጠራ፣ በአሰራር፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሀይል ልማትና በተለያዩ መስኮች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡
ሚዲያው እያሳየ ባለው እድገትና እየፈጠረ ባለው ተፅዕኖ በከተማ አስተዳደሩ ተቋማትና በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ ከሰሞኑም የትውልድ ድምፅ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በትምህርት ዘርፉ ላበረከተው አስተዋፅኦ ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ “የላቀ ትጋት ለትምህርት ጥራት”’ በሚል መርህ በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ500 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የእውቅና መርሃ ግብር ባካሄደበት ወቅት በዘርፉ አስተዋጽኦ ላደረጉ ተቋማት እውቅና ሲሰጥ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክንም እውቅና ሰጥቶታል፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም በዕውቀት የተገነባ ትውልድ ለመፍጠር ባደረገው አስተዋፅኦ ነው በከተማ አስተዳደሩ ልዩ ተሸላሚ መሆን የቻለው፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር በአዲሱ የAMN PLUS የቴሌቪዥን ቻናሉ የቴሌቪዥን ትምህርት ስርጭት ዝግጅቶችን እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን የቴሌቪዥን ትምህርት ዝግጅቶችን ከ4ኛ ክፍል እስከ 8ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች፣ የሂሳብ ትምህርት በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርትን ሳምንቱን ሙሉ ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በቅርቡ መስከረም 2018 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በኃይማኖቶች መካከል መቻቻል እና መከባበር እንዲሰፍን ብሎም አንድነት እንዲጠናከር ላበረከተው አስተዋፅኦ የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እውቅና ሰጥቶታል፡፡ ሚዲያው ተቋሙ የሚያከናውናቸውን ስራዎች ከህዝብ ዘንድ በማድረስ ከፍተኛ አበርክቶ የተጫወተ ሲሆን፤ የተለያዩ ኃይማኖታዊ በዓላትን በጥራት በቀጥታ ስርጭት እና በዜናና ፕሮግራም ሽፋን በመስጠት ኃላፊነቱን በመወጣቱ ነው እውቅና ያገኘው፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ተጠሪ ከሆኑ ተቋማት አንዱ ሲሆን፤ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት በ2017 በጀት ዓመት ላሳዩት የላቀ አፈጻጸም እውቅና በተሰጠበት ወቅት ልዩ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ የተሰጠውን የምስክር ወረቀትና ሽልማት በተረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት “አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እየሰራ ባለው ስራ በየጊዜው ትላልቅ እውቅናዎችን እያገኘ ነው፡፡ ብለዋል። በአዲስ አበባ ምክር ቤት የተሰጠውን እውቅናን በተመለከተም፤ “እውቅና ተጨማሪ አደራ ማለት ነው፡፡ የተለየ ስራ ለመስራት፣ የተሻለ ውጤት ለማምጣት፣ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን የሚያሳይ ነው። እውቅናው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን ወደፊት የሚያስፈነጥር፣ እውነተኛ ተወዳዳሪና ተመራጭ ሜትሮፖሊታን ሚዲያ የመሆን ህልማችንን ለማሳካት መነሳሳት ይፈጥርልናል፡፡ በጣም ደስ ብሎናል” ብለዋል፡፡
በቅርቡ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀምን የገመገመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴም ሚዲያው የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ በዕለቱ በቀረበው ሪፖርት እንደተመላከተው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በይዘት ተደራሽነት፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በዲጂታል ሚዲያ እና የገቢ እድገት እንዲሁም በሽያጭ የተሻለ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
የምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሁሉም ዘርፍ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በምክር ቤቱ የፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ መሀመድ ገልማ (ዶ/ር)፣ ተቋሙ በአደረጃጀቱ እና በውስጥ አሰራሩ የተሻለና ዘመናዊነትን የተላበሰ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚያቀርባቸውን የይዘት ሥራዎችም አዝናኝ እና አስተማሪ መሆናቸውንና ለማህበረሰብም ተመራጭ ሚዲያ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ከሶስት ወራት በፊትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላመጡ ተቋማት እውቅና የሰጠ ሲሆን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም በበጀት ዓመቱ ባመጣው ስኬት ልዩ ተሸላሚ በመሆን እውቅና ተሰጥቶታል። አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ እና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ያሉ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ህዝብና አመራሩ በቀጥታ የሚወያይባቸው እንደ “ዋርካ” እና “አገልጋይ” የተሰኙ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ፤ ነዋሪውና አስተዳደሩን በማገናኘት ረገድ ስኬታማ ተግባር ማከናወኑንና ይህም ለእውቅና እንዳበቃው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
“እውነቱን ለመናገር ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ የሚሰሩ ሚዲያዎች ብዙ ናቸው፡፡ ሚዲያዎች የሰራናቸውን ስራዎች ለህዝብ ጆሮ በማድረስና የተዛቡ መረጃዎችን በመመከት አብረውን እየሰሩ በመሆኑ ሁሉንም እናመሰግናለን፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ግን የከተማው ሚዲያ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የዋርካ እና አገልጋይ ፕሮግራሞች የተለየ ነጥብ እንዲያገኝ ያደርጉታል፡፡ በ“አገልጋይ” ፕሮግራም ነዋሪው ያለምንም ገደብ በቀጥታ ስልክ በመግባት ጥያቄውን በማቅረብ በአመራሩ ቀጥታ ምላሽ ይሰጠዋል፡፡ በ“ዋርካ” ፕሮግራም ደግሞ ህዝብና አመራሩ ፊት ለፊት ተገናኝተው፣ ህዝብ በነፃነት ጥያቄውን የሚያቀርብበትና አመራሩ ምላሽ በመስጠት መግባባት የሚደረስበት መንገድ ፈጥሯል” ብለዋል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፡፡
የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ በበኩላቸው፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ህዝብና መንግስትን በማገናኘት፣ በሳምንት ሰባት ቀን እና 24 ሰዓት በመስራት፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ፕሮግራሞቹን ተደራሽ በማድረግ፣ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የከተማዋን በጎ ገፅታ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ይዘቶችን በማሰራጨት፣ የከተማውን ነዋሪ ጉዳዮች በተለያየ መንገድ ለአስፈፃሚው በማድረስ መፍትሔ በማሰጠት ተፅዕኖው ከፍ እያለ የመጣ ተቋም በመሆኑ ልዩ ተሸላሚ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው፣ ሚዲያው የከተማዋን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ለነዋሪው ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በይዘት፣ በአቀራረብ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሀይል እና መሰል ዘርፎች እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ተመራጭ እና ተወዳዳሪ ሚዲያ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለሚዲያው የተሰጠው እውቅናና ሽልማትም ሰራተኛውና አመራሩ እጅ ለእጅ ተያይዞ በመስራቱ የተገኘ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “ሚዲያ ወደ ህዝብ በመውረድ የህዝብን ስሜት ማዳመጥ አለበት፡፡ በአስፈፃሚውና ህዝብ መካከል አገናኝ ድልድይ በመሆን ማገልገል አለበት፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በዚህ ረገድ በተጨባጭ ሚናውን እየተወጣ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
እውቅናው አመራሩና ሰራተኛው የሚያደርገውን ጥረት በእጥፍ ወደፊት እንዲያሳድግ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ አዳዲስ ሀሳቦችን በማመንጨትና ፈጠራ በተሞላበት መንገድ በመስራት፣ ህዝብን በማሳተፍ፣ ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ በመሆን ሚዲያው ይበልጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን አመራሩና ሰራተኛው በመቀናጀት እንደሚሰሩ ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከላይ ካነሳነው በተጨማሪ በቅርብ ጊዜ በተለያዩ የከተማ አስተዳደሩና የፌዴራል ተቋማት እውቅናዎችን ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ