የመዲናዋ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

You are currently viewing የመዲናዋ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

በአዲስ አበባ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ባሳለፍነው ሳምንት ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡ ከተሰናዱ ዋና ዋና ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የመጻሕፍት ምረቃ፣ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ ጥበባዊ ውይይቶች፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡ 

መጻሕፍት

ባሳለፍነው ሳምንት ለንባብ የበቃው የወጣቱ ደራሲ ይስሃቅ አብርሃም ‘ካፌ ጎልጎታ’ መጽሐፍ ይመረቃል፡፡ ዛሬ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ ለገሀር አቢሲንያ ባንክ ጎን በሚገኘው ጫካ ቡና ውስጥ እንደሚመረቅ ደራሲው በማህበራዊ የትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡ የተለያዩ ደራሲያንና ገጣሚያን በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ “ካፌ ጎልጎታን…በቡና ጨዋታ ፣ በጃዝ ሙዚቃ ፣ ስለ መጽሐፉ ትንሽ በማውጋት አብረን እንመርቀው” ሲል ደራሲው ጋብዟችኋል።

‘የሕይወት ትሩፋት’ መጽሐፍ ይመረቃል፡፡ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አስተባባሪነት የታተመው መጽሐፍ ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት (ወመዘክር) ብላቴን ጌታ ኅሩይ አዳራሽ ውስጥ ይመረቃል፡፡ ደራሲ ሃይለመለኮት መዋዕልና ደራሲ የዝና ወርቁ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

በእውቁ ኢትዮጵያዊ የእግር ኳስ ተጨዋች መንግስቱ ወርቁ ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው ‘መንግስቱ ወርቁ የእግር ኳስ ዕንቁ’ የተሰኘው መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ የህይወት ታሪክ መጽሐፉ የተዘጋጀው በዶ/ር ሰለሞን በርሄ ሲሆን፣ መጽሐፉ የመንግስቱ ወርቁን ህይወት በጊዜው ከነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ጋር በማዋዛት የቀረበበት ነው ተብሏል፡፡  

ቴአትር

“በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ” ቴአትር ነገ  ይመለሳል፡፡ በውድነህ ክፍሌ ተደርሶ በተሻለ አሰፋ የተዘጋጀው “በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ” ቴአትር ነገ  ጥቅምት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ዘወትር እሁድ በ8:00 ሰዓት በሀገር ፍቅር ቴአትር በድጋሚ መቅረብ እንደሚጀምርም ኤቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል፡፡ በዕውቁ ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ ህይወት ላይ የሚያጠነጥነው “በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ” ቴአትር ከዚህ ቀደም ለመድረክ በቅቶ በተመልካቾች የተወደደ ቴአትር እንደነበር አይዘነጋም፡፡ 

የቴአትር መርሃ ግብር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ፡፡ 12ቱ እንግዶች የተሰኘው ቴአትር ቅዳሜ 8:30 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይታያል፡፡ 11፡30 ሰዓት ደግሞ ባሎችና ሚስቶች  የተሰኘው ቴአትር በዚያው በብሔራዊ ቴአትር ይታያል፡፡ እሁድ በ8፡30 ሰዓት ደግሞ ንጉሥ አርማህ ቴአትር፣ እንዲሁም  እምዬ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ በዚሁ በብሔራዊ ቴአትር 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል፡፡

በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ደግሞ እሁድ በ8:00 ሰዓት በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ የተሰኘው ቴአትር ይታያል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ ቀናት በብሔራዊ ቴአትር የሚታዩት ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ  11:30 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በብሔራዊ ቴአትር  ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review