ስኬታማዎቹ የጎዳና ላይ አትሌቶች

You are currently viewing ስኬታማዎቹ የጎዳና ላይ አትሌቶች

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ፓናል በዓመቱ ውስጥ አስደናቂ ብቃት ያሳዩ አትሌቶችን ለይቶ በትራክ፣ በሜዳ እና ከስታዲየም ውጭ የሚደረጉ  ዋና ዋና ውድድሮች በሶስቱ የሽልማት ምድቦች እጩዎችን አወዳድሮ ይሸልማል፡፡ ይህ ሽልማት ቀደም ሲል በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት አሸናፊ ይሰጥ የነበረ ሲሆን፣ ከ2023 ዓ.ም ጀምሮ በሦስት ምድቦች (የትራክ፣ የፊልድ እና ከስታዲየም ውጭ) ተከፋፍሎ ይሰጣል።

እጩዎችን ለመሸለም የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት 50 በመቶ፣ የዓለም አትሌቲክስ ቤተሰብ 25 በመቶ ድምጽ እና በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰጥ የህዝብ ድምጽ 25 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው የፌዴሬሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡

የዓመቱ የዓለም አትሌት (World Athlete of the Year) ሽልማት በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (World Athletics) የሚዘጋጅ ዓመታዊ ሥነ-ስርዓት ሲሆን፣ ለሯጮች ትልቁን ዓመታዊ እውቅና ይሰጣል። በውስጡም የዓመቱ የጎዳና ላይ ምርጥ አትሌት (Out of Stadium Athlete of the Year) የሚባል የተለየ ምድብ ያካተተ ሲሆን፣ ይህ ሽልማት በተለይ በመንገድ ላይ ለሚደረጉ ውድድሮች (ማራቶን፣ ግማሽ ማራቶን፣ 10 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሩጫ) እና የእግር ጉዞ ውድድር የላቀ ውጤት ላመጡ ሯጮች ይበረከታል። እንደ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ያሉ የረጅም ርቀት ተወዳዳሪ አትሌቶች በዚህ ምድብ ተደጋጋሚ አሸናፊዎች ናቸው።

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የ2025 የዓመቱ የጎዳና ላይ ምርጥ አትሌት ዕጩዎችን ይፋ አድርጓል። እነዚህ ዕጩዎች የተመረጡት በዓመቱ ውስጥ በጎዳና ላይ ሩጫዎች ማለትም በማራቶን፣ በግማሽ ማራቶን፣ በ5 ኪሎ ሜትር፣ 10 ኪሎ ሜትር እና የእርምጃ ውድድሮች ባስመዘገቡት ስኬት ነው፡፡

የ2025 የዓመቱ የጎዳና ላይ ምርጥ አትሌት ዕጩዎች ውስጥ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ እና አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በሁለቱም ፆታ ምርጥ ብቃት ካሳዩ አምስት አትሌቶች መካከል ሆነዋል። የሴቶች ዕጩዎች ዝርዝር አምስት ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል ሦስቱ አፍሪካውያን ናቸው። ከእጩዎቹ መካከል አንዷ የ2025 የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ትዕግስት አሰፋ ናት፡፡ አትሌቷ ከሁሉም ተወዳዳሪዎች የተለየች የሚያደርጋት በዚሁ ውድድር በሴቶች ብቻ በተደረገ ሩጫ የዓለም ክብረወሰን ማስመዝገቧ ነው።

ከዚህ ታሪካዊ ስኬት በተጨማሪም በቶኪዮ 2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አግኝታለች። በሜዳሊያ ብዛት ብታንስም፣ በለንደን ያስመዘገበችው ክብረወሰን ለሽልማቱ የላቀ ዕድል ሰጥቷል። አትሌት ትዕግሥት አሰፋ በውድድር ዓመቱ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ የለንደን ማራቶን አሸናፊ መሆኗም ይታወሳል። በተጨማሪም በሴቶች ብቻ (በሴት አሯሯጮች ብቻ) በተደረገው ማራቶን የዓለም ክብረ ወሰንን በእጇ ያስገባችበት ዓመት ሆኖ አልፏል።

ከአትሌት ትዕግሥት አሰፋ በተጨማሪ ከኬንያውያኑ አትሌቶች ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና አግኔስ ንጌቲች፣ ለኔዘርላንድስ ከምትሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሲፈን ሀሰን እና ስፔናዊቷ ማሪያ ፔሬዝ ምርጥ አምስት ውስጥ የተካተቱ አትሌቶች ናቸው።

ኬንያዊቷ አትሌት ፔሬስ ጄፕቸርቸር በቶኪዮ 2025 የዓለም ማራቶን ሻምፒዮን በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደች ሲሆን፣ ይህም ለአሸናፊነት ግምት እንድታገኝ አድርጓታል፡፡ ሌላኛዋ ኬንያዊት አግነስ ንጌቲች በ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የዓለም ክብረወሰን አስመዝግባለች። እንደዚሁም ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፈን ሀሰን በሲድኒ ማራቶን አሸናፊነት እና በለንደን ማራቶን ሦስተኛ በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የብቃት ደረጃ አሳይታለች። በዘንድሮው የውድድር ዓመት ያልተሸነፈችው ስፔናዊቷ ማሪያ ፔሬዝ በ20 ኪሎ ሜትር እና በ35 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር ድርብ የዓለም ሻምፒዮን ውድድሮች ውስጥ ትልቅ የበላይነት አሳይታለች።

በወንዶቹ ምድብ እንደዚሁ አፍሪካውያን አትሌቶች ቀዳሚ ሲሆኑ፣ ከ5ቱ እጩዎች ሦስቱ ምሥራቅ አፍሪካን የወከሉ አትሌቶች ናቸው። አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ከብራዚላዊው አትሌት ካይኦ ቦንፊን፣ ካናዳዊው አትሌት ኢቫን ዱንፊ፣ ኬንያዊው አትሌት ሳባስቲያን ሳዌ እና ከታንዛኒያዊው አልፎንስ ሲምቡ ጋር ምርጥ አምቱ ውስጥ ገብቷል። አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በዓመቱ በ5 ኪሎ ሜትር 6ኛውን የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን በ10 ኪሎ ሜትርም ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።

አትሌት ዮሚፍ በ2025 በጎዳና ላይ አጭር ርቀቶች (5 ኪሎ ሜትር እና 10 ኪሎ ሜትር) የዓመቱን ፈጣን ሰዓቶች ማስመዝገቡ በዓመቱ ውስጥ ባለው የፍጥነት ብቃት የበላይነቱን አሳይቷል። ሌላኛው እጩ ዝርዝር ውስጥ የገባው ኬንያዊ ሰባስቲያን ሳዌ ሁለቱንም የለንደንና የበርሊን ማራቶን በማሸነፍ በዓለም የጎዳና ላይ ውድድሮች ታላላቅ ማራቶኖችን የመቆጣጠር ብቃት አሳይቷል። በዓመቱ ውስጥ የተመዘገቡት ፈጣን የማራቶን ሰዓቶችም የእርሱ መሆናቸው የአሸናፊነት ክብደቱን ይጨምረዋል።

ታንዛኒያዊው አትሌት አልፎንስ ሲምቡ በበኩሉ በቶኪዮ 2025 የዓለም ማራቶን ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ መውሰዱ ከፍተኛ ስኬት ሲሆን፣ በተጨማሪም የቦስተን ማራቶንን በሁለተኛነት ጨርሷል። እንደዚሁም ብራዚላዊው ካዮ ቦንፊም በ20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር የዓለም ሻምፒዮን መሆኑ በእርምጃ ውድድር ያለውን ብቃት በማሳየቱ በእጩነት ቀርቧል። ሌላኛው የእርምጃ ውድድር ባለድል ካናዳዊ አትሌት ኢቫን ደንፊ በ35 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ውድድር የዓለም ክብረወሰንና የዓለም ሻምፒዮንነትን በማስመዝገብ በዘርፉ ታላቅ ስኬት አስመዝግቧል።

በወንዶች አትሌት ታምራት ቶላ በሴቶች አትሌት ሲፈን ሀሰን በ2024 ዓ.ም የዓለም አትሌቲክስ የዓመቱ ምርጥ ከስታዲየም ውጭ የሚደረጉ ውድድሮች አትሌት አሸናፊዎች መሆናቸው ይታወሳል፡፡

ከእጩዎች መካከል የዓመቱ ምርጥ አትሌትን ለመምረጥ በዓለም አትሌቲክስ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ማለትም (በፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ኤክስ) ገጾች ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ክፍት መሆኑ ተገልጿል። ድምፅ የመስጠት ሂደቱም የሚጠናቀቀው ጥቅምት 23 ቀን 2018 ዓ.ም መሆኑን እና አሸናፊዎች ይፋ የሚደረጉትም ህዳር 21 ቀን 2018 ዓ.ም ስለመሆኑ ተመላክቷል።

በዓለም አትሌቲክስ በየዓመቱ ከሚሰጠው “የዓመቱ ምርጥ አትሌት” ዋና ሽልማት እስካሁን ድረስ አምስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያሸነፉ ሲሆን፣ በወንዶች ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ሲያሸንፉ በሴቶች መሰረት ደፋር፣ ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና የዓመቱ ምርጥ አትሌት ሽልማትን ያሸነፉ አትሌቶች ናችው፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review