ወጣቶች ሀገር በቀል የሠላም እሴቶችን በማጎልበት ሰላምና አብሮነትን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የሃይማኖትና የሠላም እሴት ግንባታ ዘርፍ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር በመቀናጀት “ሀገር በቀል የሠላምና የመቻቻል እሴቶች ለትውልድ ግንባታ ያላቸው ፋይዳ” በሚል መሪ ሃሳብ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ ሀገር በቀል የሠላምና የመቻቻል እሴቶች ለትውልድ ግንባታ ያላቸውን ፋይዳ የተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡
ወጣቶች ሀገር በቀል የሠላምና የመቻቻል እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ በማሸጋገር ሂደት ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ መድረክ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የሃይማኖትና የሠላም እሴት ግንባታ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ብረሃኑ ረታ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ቢሮ ሃላፊው አክለውም፣ ወጣቱ ችግሮች ሲያጋጥሙ በውይይት የመፈታት ባህልን የማዳበር እና ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ አላማ ማዋል እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ በረከት ቢርቢርሳ በበኩላቸው፣ በከተማዋ ወጣቶች በሰላም ግነባታ ላይ የደርሻቸውን እንዲወጡ ለማሰቻል እየተሰራ መሆኑን አሰታውሰው፣ መድረኩ ወጣቶች የሰላምና የአብሮነት አምባሳድር እንዲሆኑ የሚያነሳሳችው ነው ብለዋል፡፡
ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች እንደገለጹት፣ መድረኩ ችግሮች ሲያጋጥሙ በውይይት የመፍታት ባህልን ያዳበሩበት እና ሀገር በቀል የሠላምና የመቻቻል እሴቶችን ጠብቀው ለትውልድ ለማሻገር ሚናቸውን እንዲወጡ እንዳገዛቸው ገልጸዋል፡፡
በመሃመድኑር አሊ