ከአንገት በለይ ስፔሻሊስት ሐኪሞችን የያዘው የስዊዲን የህክምና ልዑክ ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡
የልኡክ ቡድኑ ከየካቲት12 ሆስፒታል ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያውያን የአንገት በላይ በተለይም የጆሮ ህክምናን በነጻ እንደሚሰጥ ተገልጿል።
የልኡኩ መሪና በስዊዲን የኢ ኤን ቲ ፕላስ በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ፕሬዘዳንት የሰርጀሪካል ሩም ስፔሻሊስት የሆኑት ዘውዱ መላኩ እንደገለጹት፣ ማህበሩ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለኢትዮጵያዊያን ነጻ የህክምና አገልግሎትን ለመስጠት የተቋቋመ መሆኑንና ላለፉት 13 አመታትም ይህንን ተግባር ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸው፣ በዚህ ዙር በተለይም የጆሮና የጉሮሮ ቀዶ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያዊያን አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
የልኡክ ቡድኑ ከህክምና አገልግሎት ባሻገር የሙያ ሽግግርንም ጭምር የሚሰራ መሆኑንና በዚህም ትልቅ ለውጥ መኖሩን ተናግረዋል።
ህክምና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ኢ ኤን ቲ በጎ አድራጎ ድርጅት ላለፉት 13 አመታት ባከናወነው የበጎ አድራጎት ተግባር በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ውስጥ የራሱን አሻራ እያሳረፈ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የየካቲት 12 ሆስፒታል የአንገት በላይ ቀዶ ህክምና ሰርጂን ዶ/ር ካሳዬ አሽኔ ናቸው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የማይሰጡ ህክምናዎችን በውጪ ሐገር በተለይም በአዉሮፓ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበር ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር የህዝብ ግንኙነት አቶ አብርሐም ጥላሁን፤ ሌሎች መሰል በጎ ስራን መስራት ለሚፈልጉ ዲያስፖራዎችም ጥሪ አቅርበዋል።
የልኡክ ቡድኑ አባላቱም ካላቸው ጊዜ ቀንሰው ይህንን ስራ በመስራታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ልኡክ ቡድኑ ለሚሰጠው የቀዶ ህክምና አገልግሎት መሳሪያዎችን ይዞ የመጣ ሲሆን ተልእኮውን አጠናቆ ሲመለስ የህክምና መሳሪያዎቹን ለሆስፒታሉ እንደሚያበረክትም ተመላክቷል።
በሔኖክ ዘነበ