በኮሪደር ልማቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር እና እያደረሷቸው ያሉ ጉዳቶችን ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡
አጥፊ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠርና አደጋውን ለመከላከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ክትትልና ቁጥጥሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው መምሪያው፤ በ2018 የበጀት ዓመት በአንደኛው ሩብ ዓመት በአዲስ አበባ 8ሺ 853 የንብረት አደጋ መድረሱን እና ይህም ከፍጥነት ወሰን ገደብ በላይ አልኮል መጠጦችን ጠጥቶ ማሽከርከርና ያለመንጃ ፈቃድ ማሽከርከር ለአደጋው መባባስ ምክንያት እንደሆኑ ጨምሮ ገልጿል፡፡
በሩብ ዓመቱ በከተማዋ 172 አሽከርካሪዎች ከመጠን በላይ አልኮል ጠጥተው ሲያሽከረክሩ የተገኙ ሲሆን፣ 14ሺ 695 ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከርና 1ሺ 171 ደግሞ የመንጃ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲያሽከረክሩ ተገኝተው ተገቢው ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መረጃ አመላክቷል፡፡
በአደጋው በሰዎች ህይወትና አካል ላይ ከደረሰው ከፍተኛ ጉዳት በተጨማሪ በህዝብና በመንግስት ንብረቶች ላይም ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ እና በተለይም የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ እንዲያስችሉ ታቅዶ በርካታ ወጪ ወጥቶባቸው በለሙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ላይ አደጋው እየተባባሰ መምጣቱ ተገልጿል፡፡
የቦሌ ኤርፖርት መንገድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ከለሙ መንገዶች አንዱ ቢሆንም በግዴለሽነትና በተለይም አልኮል ከመጠን በላይ ጠጥተው ሲያሽከረክሩ በነበሩ አሽከርካሪዎች መንገዱን ለማስዋብ በተተከሉ የውበት ዛፎች ላይ፣ በከፍተኛ ወጪ በተሰሩ የኤሌክትሪክ መሰመሮች እና ንብረቶች እንዲሁም በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የፖሊስ መምሪያው አስታውቋል፡፡
ስለዚህም ፖሊስ ከተማዋን ለማዘመን እና ለማስዋብ በለሙ የኮሪደር ልማቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር እና እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችን ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ግልጾ፣ አጥፊ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠርና አደጋውን ለመከላከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ክትትልና ቁጥጥሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ፖሊስ አሽከርካሪዎችም ሆኑ ባለንብረቶች እየደረሰ ያለውን አደጋ ከመከላከል አንፃር ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ማሳሰቡን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በላከው መልዕክት አስታውቋል፡፡