የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ተቋማት የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ-አውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም ከነገ ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም ጀምሮ በፈረንሳይ ፓሪስ ይካሄዳል፡፡
ፎረሙ የሁለቱን አካላት ግንኙነት ለማጠናከር እና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል፡፡
በዚህም የፈረንሳይ ድርጅቶች በአለም አቀፍ ደረጃ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚሰራ እና የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በሚደግፈው ሜዴፍ ኢንተርናሽናል እና በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን በአራት የኢንቨስትመንት ዘርፎች ማለትም በአቪየሽን፤ በታዳሽ ሃይል፤ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መሰረተልማት እና በዲጂታል ቴሌኮሙኒኬሽን ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እና እያደረገች ያለውን ሪፎርም በማሳየት የንግድ ትብብርን ለማጠናከር እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እድል እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡
እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ለሀገሪቱ ቀጣይነት ያለውን እና አካታች ልማትን ለመደገፍ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ያግዛል ተብሏል።
ፎረሙን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ፎረሙ አውሮፓ እና ኢትዮጵያን በፈጠራና በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር አካታች የሆነ እድገት ለማምጣት ትልቅ እርምጃ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፣ኢትዮጵያ በአዲስ የእድገትና የልማት ዘመን ላይ መሆኗን በመግለፅ፥ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የ10 አመቱ የልማት እቅድን በመተግበር የማይናወጥና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኑን ተናግረዋል።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የግል ዘርፉ ደግሞ ይህንን የልማት እቅድ ለማሳካት ዋና የልማት አጋር መሆኑን አብራርተዋል።
የሜዴፍ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፊሊፕ ጉቶር በበኩላቸው፥ የአውሮፓ የንግድና ኢንቨስትመንት ተቋማት ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እንዳላት ይገነዘባሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር ብቻ ሳትሆን በአረንጓዴ ልማት ፣ዲጂታል እና ትራንስፖርት መሰረተ ልማት ለመገንባት ባላት አቅም ተመራጭ መሆኗን ጠቁመዋል።
የአውሮፓ ህብረት እና ኢትዮጵያ የንግድ፣ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጎልበት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸው ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ- የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ፎረምም ይህንን እያደገ ያለ ትብብር ያሳያል መባሉ ተዘግቧል።