በምዕራባዊ ኬንያ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ 21 ሰዎች መሞታቸውን የኬንያ መንግስት አስታውቋል።
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ 25 ሰዎች የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ሲያስተናግዱ 30 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁን አመላክቷል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመታደግ እየተደረገ በሚገኘው ጥረት የኬንያ ቀይ መስቀል ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ሆኖም አደጋው እና ዝናቡ ባስከተለው ጎርፍ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ጉዳት ስለደረሰባቸው የነፍስ አድን ስራውን አዳጋች አድርጎታል ነው የተባለው።
በዚህ የተነሳም የኬንያ መንግስት በትላንትናው ዕለት የነፍስ አድን ስራውን ለማቋረጥ ተገዶ የነበረ ቢሆንም በዛሬው ዕለት በሕይወት የሚገኙ ሰዎችን እና ሌሎች ተጎጂዎችን የማፈላለግ ስራ መቀጠሉን ቢቢሲ አስነብቧል።
ከዚህ ባለፈም በአደጋው ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች የምግብ እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ የፖሊስ እና ወታደራዊ ሄሊኮፕተሮች መሰማራታቸው ተሰምቷል።
ኡጋንዳ ከኬንያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ ባሳለፍነው ረቡዕ በተመሳሳይ ደራሽ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ባስከተሉት አደጋ የሰው ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
በዳዊት በሪሁን