የራስ ምታት ህመም ከሌላ በሽታ ጋር በተጓዳኝ ወይም ራሱን ችሎ ሊከሰት ይችላል።
ራሱን ችሎ የሚከሰት ራስ ምታት የመጀመሪያ ደረጃ ሲባል፤ ከሌሎች በሽታዎች ጋር በተጓዳኝ የሚከሰተው ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ በመባል ይታወቃል።
ማይግሪን የራስ ምታት ህመም ከመጀመሪያ ደረጃ የራስ ምታት ህመም አይነት ይመደባል።
የማይግሪን የራስ ምታት ህመም መንስኤዎች፣ ምልክቶች፣ ህክምናና የመከላከያ መንገዶቹን በተመለከተ በዳግማዊ ሚኒሊክ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆሲፒታል ሀኪም የሆኑት (ዶ/ር) ዮርዳኖስ መንግስቱ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የማይግሪን ራስ ምታት ህመም ምልክቶች
የማይግሪን ራስ ምታት ህመም ያለባቸው ሰዎች ህመሙ ከመጀመሩ ከ24 እስከ 48 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ የምግብ ፍላጎት መጨመር በተለይ ጣፋጭ ምግቦችን መመገብ፣ መነጫነጭ እና መበሳጨት ይስተዋልባቸዋል።
ህመሙ ሊጀምር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ሜይግሪን አውራ ይባላል፤ በዚህ ጊዜ አይን ላይ ነጫጭ ነጠብጣቦችና ዝግዛግ ቅርፅ ያላቸው ብርሃናማ ምልክቶች መታየትና ድምጽ ቶሎ ለመስማት መቸገር ያጋጥማል። ዋናው የራስ ምታት ህመም በሚጀምርበት ወቅት ደግሞ በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው እና ያልተለመደ የህመም ስሜት ይኖረዋል።
ህመሙ ጭንቅላትን ለሁለት ከፍሎ በአንድ በኩል የሚያም ሲሆን ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ ብርሃን ለማየት እና ድምጽ ለመስማት ያለመድፈር ስሜቶች ይኖሩታል።
በዚህ ምክንያት በህመሙ የተጠቁ ሰዎች ፀጥ ያለ ቦታን፣ ጨለማንና ብቻቸውን መሆንን ይመርጣሉ።

ህመሙ አስከ 3 ቀን ሊቆይ የሚችል ሲሆን የህመሙ ስሜት ከለቀቀ በኃላም ከፍተኛ የሆነ የድካም፣ የሰውነት መዛልና የትኩረት ማጣት ችግሮች ያጋጥማሉ።
የማይግሪን ራስ ምታት ህመም መንስኤዎች
የሥራ ጫና እና ጭንቀት እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሱ ሲሆን የእንቅልፍ ማጣት፣ የረሀብ ስሜት፣ የአልኮል መጠጥ፣ ሲጋራ እና በተለየ ሴቶች በወር አበባ ሂደት ጊዜ የሆርሞን መለዋወጥ ለማይግሪን ራስ ምታት ህመም መንስኤ ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል።
የማይግሪን ራስ ምታት ህመም ህክምና

ህመሙ በመድሃኒት እና ያለመድሃኒት የሚታከም ሲሆን ህክምናው ህመሙን የሚያድን ሳይሆን የህመም መጠኑን የሚቀንስ ነው።
ህክምናው በመርፌ እና በኪኒን መልክ የሚሰጥ ሲሆን ከሰዓታት ማስታገሻ ጀምሮ እስከ 6 ወር ቅድመ ህመም መከላከያ መድሀኒት ይሰጣል።
ህመሙን የሚያባብሱ ነገሮችን ለይቶ በማወቅ ቶሎ ቶሎ እንዳይከሰት ጥንቃቄ በማድረግ ያለህክምና ህመሙን ማስታገስ ይቻላል።
የማይግሪን ራስ ምታት ህመም መከላከያ መንገዶች
ቋሚ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እና ህመሙን የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ለይቶ በማወቅ ጥንቃቄ ማድረግ የማይግሪን ራስ ምታት ህመም ቶሎ ቶሎ እንዳይነሳ ለማድረግ እንደሚረዳ (ዶ/ር) ዮርዳኖስ መንግስቱ ሙያዊ ምክር ሰጥተዋል ።
በበረከት ጌታቸዉ