በአፍጋኒስታን በተከሰተ ርዕደ መሬት ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተሰማ

You are currently viewing በአፍጋኒስታን በተከሰተ ርዕደ መሬት ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተሰማ

AMN – ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም

በሰሜናዊ አፍጋኒስታን በ6.3 ማግኒትዩድ የተመዘገበ ርዕደ መሬት ተከስቶ ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።

ማዛር ሻሪፍ በተባለው 500 ሺህ ሰዎች የሚኖሩበት የአፍጋኒስታን ትልቅ ከተማ አጋጥሟል የተባለው አደጋ ከመሬት 28 ሜትር ጥልቀት ላይ የተከሰተ መሆኑን የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ ጠቁሟል።

እሁድ ለሰኞ አጥቢያ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከሞቱ 20 ሰዎች በተጨማሪ ከ320 በላይ ሰዎች መጠኑ የተለያየ ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

በህንጻ ፍርስራሾች ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለማትረፍ የሚደረገው የነፍስ አድን ስራ አሁንም ሲቀጥል፤ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ስካይ ኒውስ አስነብቧል።

አፍጋኒስታን በተደጋጋሚ በሚከሰቱ የርዕደ መሬት አደጋዎች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቂ ከሆኑ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ ናት።

ባሳለፍነው ታህሳስ በአፍጋን ተራራማ አካባቢዎች በ6.0 ሬክተር ስኬል የተለካ ተመሳሳይ አደጋ ተከስቶ ከ1 ሺህ 400 በላይ ሰዎች ሲሞቱ 3250 በሚሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

በተመሳሳይ በ2023 ባጋጠመ አደጋ ከ2445 በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review