የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የሰሜን ዕዝ ዝክረ ሰማዕታትን ለመዘከር በተዘጋጀው የመታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ሠራዊቱ ከየትኛውም አቅጣጫ በየትኛውም ጊዜ በልማታችን ፣በሰላማችን እና በብሄራዊ ጥቅማችን ላይ ሊቃጣ የሚችል ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።
ከሃዲው ህወሃት መከላከያ ሠራዊት ለሀገሩ ክብር የከፈለውን መስዋዕትነት ክዶ ኢ -ሰብዓዊ በሆነ መንገድ ክብሩን አዋርዶ ከሰው ልጅ አዕምሮ በላይ የሆነ ግፍና ጭካኔ መፈፀሙን አውስተዋል።
ይህ ድርጊት መላው ሰራዊቱን እና መላው የኢትዮጵያን ህዝብ ያሳዘነና አንገት ያስደፋ ድርጊት በመሆኑ መቼም የትም እንዳይደገም መቼም አንረሳውም በሚል መሪ ቃል ቀኑ በልዩ ሁኔታ መታሰቡንም አንስተዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ሰውን በዘረኝነት እና በጥላቻ ቀስቅሰው እና አነሳስተው ከጠላት ተዋግቶ ነፃ ያወጣቸውን፣ አንበጣ እያባረረ ሰብላቸውን የሚሰበስብላቸውን ህዝቤ ነው ብሎ ደክሞት ያረፈን የመከላከያ ሠራዊት በተኛበት ክህደት መፈፀማቸው በጣም ያማል ብለዋል።
ይህ ድርጊት በተፈፀመበት ወቅት የኢትዮጵያ ሰራዊት ተገዶ የህልውና ዘመቻ በጀመረበት እና ትግራይ ውስጥ በገባበት ወቅት አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ሰራዊቱ እንደተበደለ እና እንደተካደ ያውቅ ስለነበር ከሰራዊቱ ጎን ይቆም እንደነበርም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታውሰዋል።
ዛሬም ቢሆን ይህ የከሃዲዎች ስብስብ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ትላንትና እታገልልሃለሁ ብሎ ልጆቹን ከጉያው ነጥቆ እየወሰደ አስጨፍጭፎ ባዶውን ያስቀረውን የትግራይን ህዝብ ከመካስ ይልቅ ዳግም ለሌላ እልቂት እየተዘጋጀ እና የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም መላው የትግራይ ህዝብ ትላንትና የደረሰበት ግፍና መከራ ዛሬም እንዳይደገም በቃ ሊልና ራሱን ነፃ ሊያወጣ ይገባዋል ማለታቸዉን የሃገር መከላከያ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል።