ላለፉት አስር አመታት በዋነኛነት የዱር እንስሳት መመናመንን እና የተፈጥሮ መዛባትን ለማስቀረት ሲሰራ የቆየው የአለም የዱር ህይወት ፕሮግራም 25ተኛ አመታዊ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።
ለ አምስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ከ38 የአለም ሀገራት የተውጣጡ ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒሰትር ዲኤታ ስለሺ ግርማ፤ የዱር እንስሳትና የተፈጥሮ ሀብቶች ለሰው ልጆች መኖር አስፈላጊ በመሆናቸው ተስማሚ ስነ ምህዳር መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን በዚሁ ወቅት ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአካባቢውን ማህበረሰብ የኑሮ ዘይቤ ማሻሻል ላይ ትኩረት በመስጠት አዳዲስ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ጭምር የተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ የዱር እንስሳት ጥበቃ ስራ ድንበር ተሸጋሪ መሆኑን የገለጹት ሚኒስቴር ዲኤታው፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ያከናወነቻቸውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች በተመለከተ ልምዷን ታካፍላለች ብለዋል፡፡
የዱር እንስሳት ጥበቃ ስራ በመንግስት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ባለሙያው ዶ /ር ፋኑኤል ከበደ ናቸው።
ባለሙያው አሁን ላይ ተጨባጭ ለውጦች እይታዩ መሆናቸውን ገልፀው፤ ይህን ለማስቀጠል የሁሉንም ህብረተሰብ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን አመላክተዋል ።
በጸጋ ታደለ